በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ የሚገኘው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት አካል የሆነው "የውሃ ቀን" በይፋ ተከፈተ

በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ የሚገኘው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት አካል የሆነው "የውሃ ቀን" በይፋ ተከፈተ

አዲስ አበባ — ጥቅምት 18 / 2019 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ)

በአዲስ አበባ የሳይንስ ሙዚየም በተለያዩ ሁነቶች እየተካሄደ የሚገኘው 3ኛው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት በሦስተኛ ቀኑ የዘርፉን ዋነኛ ምሰሶ ትኩረት ያደረገውን “የውሃ ቀን” ማክበር ጀምሯል።

በመድረኩን የከፈቱት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሳኒቴሽን መሠረተ ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ኑረዲን መሐመድ የዘንድሮውን የውሃ ቀን ማዕከላዊ ጭብጥ ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ መሪ ቃሉም “ ከማስረጃ ወደ ተግባር - ለተቀናጀ የውሃ እና የውሃ ሀብት አስተዳደር በሳይንስ ላይ የተመሰረቱ መፍትሄዎች!” የሚል ነው።

ይህ መሪ ሀሳብ ሳይንሳዊ እውቀት፣ አስተማማኝ መረጃ፣ ፈጠራ እና ጠንካራ ሽርክናዎች ከምርምርና ከንድፈ-ሀሳብ ባለፈ የሰዎችን ሕይወት የሚያሻሽሉ፣ የውሃ ደህንነትን የሚያጠናክሩ እና አካባቢን የሚጠብቁ ተግባራዊ መፍትሄዎች መሆን እንዳለባቸው የሚያሳስብ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ስራ አስፈጻሚው አክለውም ውሃ ለሕዝብ ጤና፣ ለምግብ ዋስትና፣ ለአካባቢ ዘላቂነት እና ለሰብአዊ ክብር መሠረታዊ መሆኑን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ንጽህና (WASH) ዘርፍ ወሳኝ በሆነ የለውጥ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ፈጣን የሆነ የከተሞች መስፋፋት፣ የህዝብ ቁጥር መጨመር እና እየጨመረ የመጣው የአየር ንብረት አደጋዎች (ተደጋጋሚ ድርቅና ድንገተኛ ጎርፍ) ከገለልተኛ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ባሻገር የወንዝ ተፋሰሶችን እና የከርሰ ምድር ውሃን በጋራ ወደሚያስተዳድሩ የተቀናጁና ለአየር ንብረት መቋቋም የሚችሉ ዘላቂ መፍትሄዎች እንድንሄድ ያስገድዱናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ዘርፉ

ጉልህ እድገት ቢመዘገብም፤ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ የከተማ ንፅህናን በማስተዳደር፣ በቆሻሻ ውሃ አያያዝ እና በውሃ መገልገያዎች የፋይናንስ አፈጻጸም ላይ አሁንም ክፍተቶች እንዳሉም ተመልክቷል።

አገራዊ ቁርጠኝነትን እና የዘላቂ ልማት ግብ 6ን (SDG 6) በዜጎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ማሻሻያ ለማስመዝገብ በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ፖሊሲዎች፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና ዘላቂ ፋይናንስ ወሳኝ መሆናቸውንም አቶ ኑረዲን አብራርተዋል።

በዕለቱ ይፋ በተደረገው አጀንዳ መሠረት አራት ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ክፍለ ጊዜዎች የሚካሄዱ ሲሆን፣የተቀናጀ ዕቅድ እና የአየር ንብረት መቋቋም፣ የውሃ እና የኢነርጂ ደህንነትን በዲጂታል ተፋሰስ መረጃ፣ የሃይድሮ-ክትትል እና የውሃ ጥራት ስርዓት ማሳደግ፣ዘላቂ ፋይናንስ፣ ንግድ እና ትብብርን ማጠናከር እና በተለያዩ ደረጃዎች የከርሰ ምድር ውሃ አስተዳደርን ማጠናከር ይገኙበታል።

የመጀመሪያውን የውይይት መድረክ እንዲመሩ የተጋበዙት በዩኒሴፍ (UNICEF) ኢትዮጵያ የገጠር ንፅህና አጠባበቅ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ሚስተር ካቡካ ምዋታማ ባንዳ (Mr. Kabuka Mwatama Banda) ናቸው።

በመድረኩ የሚኒስቴሩ ተወካዮች፣ ለልማት አጋሮች፣ ለዲፕሎማሲ ማህበረሰብ አባላት፣ ለተመራማሪዎች እና ለክልል የውሃ ቢሮ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

ይህ የውሃ ቀን የምክክር መድረክ በዘርፉ በተመዘገቡ ስኬቶች እና በቀሩ ክፍተቶች ላይ በጥልቀት በመምከር፣ ፖሊሲንና ኢንቨስትመንትን ሊያሳውቁ የሚችሉ ተግባራዊ መፍትሄዎችን በማስቀመጥ ረገድ ታላቅ አገራዊ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

Share this Post