ሚኒስቴሩ ቀልጣፋና ተወዳዳሪ የሥራ አካባቢ ለመፍጠር የሪፎርም ሥራዎችን አጠናክሯል
መስከረም 8፣2019 ዓ.ም. – (ው.ኢ.ሚ)
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ቀልጣፋና ተወዳዳሪ የሥራ አካባቢ ለመፍጠር በተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች ላይ መሠረታዊ ለውጦችን እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።
ሚኒስቴሩ ይህን የገለጸው ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ የሱፐርቪዥን ቡድን አባላት የሪፎርም ሥራዎቹንና በሥራ አፈጻጸም የተገኙ ውጤቶችን በሚያስመለክት ገለጻ ባቀረበበት መድረክ ነው።
የመድረኩ ዋና ዓላማ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎችን በመገምገም የተሻሉ ተሞክሮዎችን መለየት፣ በሌሎች ተቋማት ሊስፋፉ የሚችሉ አሠራሮችን ማስቀመጥ እና በሥራ አፈጻጸም የተሻሉ ተሞክሮዎችን ለመለየት እንዲቻል መሆኑ ተገልጿል።
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈጻሚና የሪፎርም ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኦልቀባ ባሼ፣ ለሱፐርቪዥን ቡድን አባላት በሰጡት ገለጻ፣ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ዘርፍ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በሚኒስቴሩ የተለያዩ የሪፎርም ፕሮግራሞች ሲተገበሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ኦልቀባ ገለጻ፣ ሚኒስቴሩ ከዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ እድገት፣ ከኢኮኖሚ ሁኔታዎችና ከኢንዱስትሪው ፍላጎት ጋር በማጣጣም የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት የሪፎርም ሥራዎቹን እያሻሻለና እያጠናከረ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይም ቀልጣፋና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎችን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን፣ ሥራዎቹ የሚኒስቴሩን የአገልግሎት አሰጣጥና የሥራ አፈጻጸም ለማሻሻል ያላቸውን ሚና አብራርተዋል።
የሱፐርቪዥን ቡድን አባላትም በመድረኩ በቀረቡት የሪፎርም ሥራዎች ላይ ምልከታና ግምገማ በማድረግ በሌሎች ተቋማት ሊስፋፉ የሚችሉ ተሞክሮዎችን ለመለየት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የሀገሪቱን ልማት ለማገዝ ቀልጣፋ፣ ተደራሽና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የሥራ አሠራር ለመገንባት የሪፎርም ሥራዎቹን ማስቀጠሉ ተገልጿል።