በኢትዮጵያ የውሃ ቧንቧ መሠረተ ልማት ጥራትና ስታንዳርድ ላይ ያተኮረ ወርክሾፕ ተካሄደ
በኢትዮጵያ የውሃ ቧንቧ መሠረተ ልማት ጥራትና ስታንዳርድ ላይ ያተኮረ ወርክሾፕ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ነሐሴ 12/2018 ዓ. (ው.ኢ.ሚ)_በኢትዮጵያ የውሃ አቅርቦት ቧንቧዎች የጥራት ደረጃን ማሻሻል፣ የተቀመጡ ስታንዳርዶችን ማስፈጸም እና ዘላቂ የውሃ መሠረተ ልማት ለመገንባት የሚያግዙ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ወርክሾፕ ተካሄደ።
ወርክሾፑ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት እና በጣና የቁፋሮ እና የቧንቧ የኢንዱስትሪዎች ኃላ.የተ.የግል ኩባንያ በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በስካይላይት ሆቴል ተካሂዷል።
የውይይት መድረኩ የኢትዮጵያን የውሃ አቅርቦት ቧንቧ መሠረተ ልማት ሥርዓት፣ የቴክኖሎጂ ምርጫ፣ የምርቶች ጥራትና ተስማሚነት፣ የጥራት ማረጋገጫ ሥርዓት እና የአጭርና የረጅም ጊዜ ወጪ ንጽጽር የተመለከቱ ጉዳዮችን አካቷል።
በመድረኩ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ፣ ጥራቱን የጠበቀ የውሃ መሠረተ ልማት መገንባት የመጠጥ ውሃ አቅርቦትንና የሳኒቴሽን አገልግሎትን ለማሻሻል ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
አምባሳደር አስፋው፣ የግሉ ዘርፍ በሀገር ውስጥ ጥራት ያላቸውን የውሃ መሠረተ ልማት ምርቶች በማምረትና በማቅረብ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ወጪ ለመቀነስ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎንና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት መካከል ያለውን ቅንጅት ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር መአዛ አበራ በበኩላቸው፣ የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ጥራት ለሕብረተሰቡ ጤና እና ለውሃ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ዘላቂነት ያለው አስፈላጊ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል። ድርጅታቸውም የምርቶችን ተስማሚነትና ጥራት የሚያረጋግጡ የምዘናና የቁጥጥር ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚቀጥል አብራርተዋል።
በወርክሾፑ የዘርፉ ባለሙያዎች የዲዛይን መርሆዎች፣ የመጠንና የውሃ ጥራት ደረጃዎች፣ የቴክኖሎጂ አማራጮችና አተገባበራቸው፣ የምርቶች ብቃትና ተስማሚነት፣ የቧንቧ ማገናኛ ዘዴዎች፣ የጥገናና የተከላ ሥራዎች፣ የምርት ደረጃዎች፣ የፍተሻ ሰርተፊኬትና የጥራት ማረጋገጫ ሥርዓቶች ላይ ሰፊ ሙያዊ ገለጻ አቅርበዋል።
በተጨማሪም የመጀመሪያ የግዢ ወጪን ብቻ ሳይሆን የተከላ፣ የጥገናና የምርት ዕድሜ ወጪዎችን በማካተት የረጅም ጊዜ ዘላቂ እሴትን በመመዘን የቴክኖሎጂና የቧንቧ ምርት ምርጫ ሊደረግ እንደሚገባ ተገልጿል።
በመድረኩ ከተነሱ ዋና ጉዳዮች መካከል በዘርፉ የተለያዩ ስታንዳርዶችና ደረጃዎች ቢኖሩም በተግባር አስገዳጅ አለመሆናቸው አንዱ ነው። የሕብረተሰቡን ጤናና የውሃ መሠረተ ልማቶችን ደህንነት ለማረጋገጥ እነዚህ ስታንዳርዶች ተገቢው የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶላቸው አስገዳጅ እንዲሆኑ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል።
በወርክሾፑ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከጣና የቁፋሮ እና የኢንዱስትሪያል ቧንቧዎች ኢንዱስትሪ እና ከኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የተወጣጡ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የውይይቱ ውጤት ለፖሊሲ ዝግጅትና ለውሳኔ ሰጪዎች ጠቃሚ ግብዓት የሚሆኑ አቅጣጫዎችና ምክረ ሀሳቦችን ያካተተ ሲሆን፣ በውሃ አቅርቦት ዘርፍ ያሉ የጥራት ክፍተቶችን በመቅረፍ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የውሃ ቧንቧ ምርቶችን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋልና የመሠረተ ልማቱን ዘላቂነት ማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ መሆኑ ተጠቁሟል።