ቀልጣፋና ተደራሽ የመንግስት አገልግሎት ላይ ስልጠና ተሰጠ

ቀልጣፋና ተደራሽ የመንግስት አገልግሎት ላይ ስልጠና ተሰጠ

ሐምሌ 11/2018 ዓ.ም ( ው.ኢ.ሚ)

ለውሃና ኢነርጂ ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈፃሚዎች፣ ሥራ አስፈፃሚዎችና ባለሙያዎች በ“ቀልጣፋና ተደራሽ የመንግስት አገልግሎት” ላይ ስልጠና ተሰጠ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ በስልጠናው መክፈቻ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የመንግስት አስተዳደር አገልግሎት ሪፎርም የዝግጅት ምዕራፍ አፈፃፀም በሲቪል ሰርቪስ ሱፐርቪዥን ቡድን ግምገማ ጥሩ ደረጃ ላይ መገኘቱን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ በዚህ ሂደት ውስጥ ለተሳተፉ፣ ሥራውን ላስተባበሩና በትጋት ላከናወኑ የዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል። ቀሪ ሥራዎችንም በተሻለ አፈፃፀም በማጠናቀቅ የዝግጅት ምዕራፉን በውጤታማነት አጠናቆ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለመሸጋገር የሰው ሀብት አቅም ማጎልበት ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በተለይም የሚሰጠው የመንግስት አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ተደራሽ፣ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥና የተገልጋዮችን ፍላጎት ያማከለ እንዲሆን የሁሉም የዘርፉ አመራርና ሠራተኛ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተጨማሪም ስልጠናው በጥብቅ ዲስፕሊን፣ በንቃት ተሳትፎና በተግባር ተኮር አቀራረብ እንዲመራ አሳስበው፣ ስልጠናውን በይፋ ከፍተዋል።

በመቀጠል ስልጠናውን የሰጡት የሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈፃሚ የስልጠናውን ሰነድ በዝርዝር በማቅረብ፣ የቀልጣፋና ተደራሽ የመንግስት አገልግሎት መርሆዎችን፣ የተገልጋይ አያያዝን፣ የአገልግሎት ጥራትን፣ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን እንዲሁም በሪፎርሙ የሚጠበቁ የአፈፃፀም ውጤቶችን አብራርተዋል።

ስልጠናው ተሳታፊዎች በየዕለቱ በሚያከናውኑት ሥራ ውስጥ የተገልጋዮችን ፍላጎት በመረዳት፣ አገልግሎትን በጊዜና በጥራት በመስጠት፣ የአሰራር መዘግየቶችን በመቀነስና የሥራ ተጠያቂነትን በማጠናከር የተሻለ የመንግስት አገልግሎት እንዲያረጋግጡ ለማስቻል ያለመ ነው።

በስልጠናው የቀረቡትን ጉዳዮች መሠረት በማድረግ ተሳታፊዎች የግልጽነት፣ የአፈፃፀም፣ የአገልግሎት ጥራትና የተገልጋይ አያያዝ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጥያቄዎችን አንስተዋል። ለተነሱት ጥያቄዎችም በቂ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

በመጨረሻም ስልጠናው ተሳታፊዎች ያገኙትን እውቀትና ግንዛቤ ወደ ተግባር በመቀየር የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ አገልግሎቶችን ይበልጥ ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ግልጽና ተጠያቂ ለማድረግ የራሳቸውን ሚና በተግባር እንዲወጡ በማስገንዘብ ተጠናቋል።

የስልጠናው ዋና ዓላማ፦ የመንግስት አገልግሎትን በተገልጋይ እርካታ፣ በቅልጥፍና፣ በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በውጤታማነት በማጠናከር የተሻለ የሥራ ባህልና የአገልግሎት አሰጣጥ ለመፍጠር ነው።

Share this Post