22ኛው የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉባኤ ተጠናቀቀ።
22ኛው የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉባኤ ተጠናቀቀ።
ሐምሌ 3፣ 2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ)
22ኛው የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር (EAPP) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉባኤ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ሲካሄድ ቆይቶ ተጠናቋል።
በጉባኤው በቀጣናውና በጎረቤት ሀገራት መካከል የኤሌክትሪክ ትስስርን ማጠናከር፣ የኃይል ንግድን ማስፋፋት፣ የተቀናጀ የክልላዊ የኃይል ገበያን መገንባት እና የታዳሽ ኃይል ልማትን ማበረታታት በተመለከተ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።
ከጉባኤው በፊት 37ኛው የስቲሪንግ ኮሚቴ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ያደረገው ውይይትና ያቀረበው ሪፖርት ለሚኒስትሮች ምክር ቤቱ ውሳኔዎች መሠረት ሆኗል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ በጉባኤው መጠናቀቂያ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር (EAPP) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበርነትን ከግብፅ በይፋ መረከቧን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ የሊቀመንበርነት ሽግግሩ አባል ሀገራት የሚኒስትሮች ምክር ቤቱን በየዓመቱ በመፈራረቅ የሚመሩበት አሠራር አካል ነው።
ኢትዮጵያም በአዲሱ የሊቀመንበርነት ዘመን የቀጣናውን የኃይል ትስስር ለማጠናከር፣ የኤሌክትሪክ ግብይትን ለማስፋፋት እና የታዳሽ ኃይል ልማትን ለማበረታታት ከአባል ሀገራት ጋር በቅርበት እንደምትሰራ አስታውቀዋል።
በ37ኛው የስቲሪንግ ኮሚቴ ሪፖርት መሠረትም የተቋማዊ አሰራር ማሻሻያዎች፣ የክልላዊ የኃይል ገበያ ልማት እና የአባል ሀገራት ትብብርን የሚያጠናክሩ ዕቅዶች በጋራ ተገምግመዋል።
ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ እንደገለጹት፣ በጉባኤው ከፍተኛ ውይይት ካስነሱ ጉዳዮች መካከል የኤሌክትሪክ የኃይል ገበያ ማዕከል ዋና መቀመጫን የመወሰን ጉዳይ ይገኝበታል።
በተለይም የገበያ ማዕከሉ አስተናጋጅ ሀገር ምርጫን በተመለከተ ከግብፅ ጋር የነበሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ሰፊ ውይይትና ድርድር መካሄዱን ጠቁመዋል።
አባል ሀገራቱ በልዩነቶች እንዳይከፋፈሉ የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻልና ማጠናከር እንዲሁም የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ወሳኝ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር (EAPP) 13 አባል ሀገራትን ያካተተ የክልላዊ ትብብር ተቋም ሲሆን፣ ዋና ዓላማው የኤሌክትሪክ አቅርቦትን በማስተሳሰር የኃይል ደህንነትን ማጠናከር፣ የኃይል ወጪን መቀነስ እና በአጎራባች ሀገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ማሳደግ ነው።