1000ኪሎ ዋት ሀይል የሚያመነጨው የሶላር ሀይል ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

1000ኪሎ ዋት ሀይል የሚያመነጨው የሶላር ሀይል ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ጀመረ።   የካቲት 10/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል ጀረር ዞን ምስራቅ ጋሻሞ ወረዳ ያስገነባውን የሶላር ሀይል ማመንጫ ፕርሮጀክት አጠናቆ ለአገልግሎት አውሏል። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ የፕሮጀክቱን ስራ መጀመር አስመልክቶ በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የጋሻሞ የሶላር ሀይል ማመንጫ ከ400 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ የተገነባና ከ6ሺ በላይ አባውራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።   በቂ አስተማማኝና አዋጭ ኢነርጂ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት መሆኑን የገለጹት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ለዚህ ደግሞ ከዋናው የሀይል መስመር ርቀው የሚገኙ አካባቢዎችን በሶላር ሀይል ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ያለው ስራ ማሳያ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ እምቅ የታጃሽ ሀይል ሀብት ባለቤት ብትሆነም እስከ ከሁን ጥቅም ላይ ማዋል የቻለችው ጥቂቱን ብቻ ነው ያሉት ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ በመንግስት በተሰጠው ትኩረት መሠረት የተጀመረውን ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ብለዋል።   እንደ ሀገር 63 ሚሊየን ዜጎችን የሀይል ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ቢሆንም 47 ሚሊየን ዜጎች እስካሁን የሀይል ተደራሽ አለመሆናቸው ትኩረት ሰጥተን ልንሰራበት የሚገባ መሆኑን አመላካች ነውም ብለዋል። አክለውም እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ የሀይል ተደራሽነትን 75 ከመቶ ለማድረስ ብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ተቀርጾ ከምን ጊዜውም በተሻለ ሁኔታ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጋሻሞ የሶላር ሀይል ፕሮጀክት ማሳያ ነው ብለዋል።   የሶላር ሀይልን ተደራሽ ስናደርግ የህዝባችን ኢኮኖሚ እያደገ ከመምጣቱም ባሻገር የበካይ ጋዝ ልቀትን ከመቀነስ አኳያ የምናበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ በመሆኑ በካርበን ፋይናንስ ተጠቃሚ እንሆናለንም ብለዋል። ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት በሶላር ሀይል የሚሰሩ የሶላር ፓምፖች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑንም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።   ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ለሱዳን ፣ ጅቡቲ ፣ ኬኒያ ፣ ለደቡብ ሱዳንና ለታነዛኒያ ተመጣጣኝ በሆነ ታሪፍ ሀይል ስታቀርብ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከማግኘት ባሻገር የቀጠናውን ሰላም በማረጋጋት በቀጣይ ህዝብና ህዝብን የሚያቀራርብ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠርም ጭምር ነው ብለዋል። በአጠቃላይ የጋሻሞ የሶላር ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለቀጣዮቹ 20 ዓመታት ለህብረተሰቡ ያልተቆራረጠ ሀይል በመስጠት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ በመሆኑ ህብረተሱ ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ ዘላቂ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አደራ ብለዋል።

Share this Post