ብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም (NEP 3.0) ፍኖተ ካርታ ላይ ውይይት ተካሄደ።

ብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም (NEP 3.0) ፍኖተ ካርታ ላይ ውይይት ተካሄደ።

ሰኔ 22/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚተገበረው ብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም (NEP 3.0) ፍኖተ ካርታ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በሂልተን ሆቴል ውይይት ተካሄደ።

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም (NEP 3.0) እ.ኤ.አ በ2035 ሁለንተናዊ አስተማማኝ፣ ተመጣጣኝ እና ዘላቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማስፈን የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ግብ ነው ብለዋል።

መድረኩ መሰረታዊ ፍላጎትን በማሟላት፤ ህይወትን በመለወጥና የኢኮኖሚ እድገትን በማጎልበት ሁሉን ያሳተፈ ኃይል ለመገንባት ያለመ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ተመጣጣኝና ቀጣይነት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት የመሰረተ ልማት ግብ ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚ እድገትና ለማህበራዊ ልማት መሰረት ነው ብለዋል።

በቀጣይም ህዝባችንን የመብራት አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ በመሆኑ፤ ባለፉት ዓመታት በብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም 1 እና ፕሮግራም 2 ከግሪድና ከግሪድ ውጪ ተደራሽነትን በማስፋት፣ ተቋማዊ አቅምን በማጠናከር እና ወሳኝ ኢንቨስትመንቶችን በማንቀሳቀስ ረገድ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱንም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል።

ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም የጥናቱ ግኝት ላይ በመወያየት ለቀጣይ ብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራምን በሁሉም የሀገራችን ክፍል የኤሌክትሪክ ኃይልን ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ የግሉ ዘርፍም ሚናው የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመድረኩ ከአለም ባንክ ተወካይ፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የልማት አጋሮችና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል።

Share this Post