ለኤረር CR-WASH ፕሮጀክት 48.7 ሚሊዮን ብር የአዋጭነት ጥናት፣ ዝርዝር ዲዛይንና የተግባር ስልጠና ውል ተፈረመ፡፡

ለኤረር CR-WASH ፕሮጀክት 48.7 ሚሊዮን ብር የአዋጭነት ጥናት፣ ዝርዝር ዲዛይንና የተግባር ስልጠና ውል ተፈረመ፡፡

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 07 ቀን 2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ)

በሱማሌ ክልል ለሚተገበረው የኤረር የአየር ንብረትን የሚቋቋም (Climate Resilient) የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን (CR-WASH) ፕሮጀክት ለማሳካት የሚያግዝ 48.7 ሚሊዮን ብር የአማካሪ አገልግሎት ውል በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መካከል ተፈርሟል።

ውሉ በConsolidated WASH Account (CWA-II) ፕሮግራም በ48,722,942.00 የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበር ሲሆን፣ ለኤረር CR-WASH ፕሮጀክት የወንዝ ውሃ መውሰጃ ሥርዓት የአዋጭነት ጥናት (Feasibility Study)፣ ዝርዝር ዲዛይን (Detailed Design) እና በዘመናዊ የሞዴሊንግ ሶፍትዌሮች የተደገፈ የተግባር (Hands-onTraining) ስልጠና ለማከናወን የሚውል ነው።

የውል ስምምነቱን የፈረሙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት በመስራት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን፣ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራዎችንና ሌሎች የውሃ ቴክኖሎጂ ተግባራትን በውጤታማነት ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ክቡር አምባሳደሩ አክለውም ኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ልምድና ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችና አሰልጣኞችን በማሰባሰብ በውሃ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ተዓማኒና ጥራት ያለው የስልጠናና የምክር አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸው፣"ኢንስቲትዩቱ በአዲስ መልክ ከተደራጀ ወዲህ ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጠንካራ የቴክኒክ ክንድ በመሆን እያገለገለ ይገኛል። ዛሬ የተፈረመው ውልም ይህንን አጋርነት ይበልጥ የሚያጠናክር እና የተቋማቱን የጋራ ሥራ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው" ብለዋል።

እንደ ክቡር አምባሳደሩ ገለጻ፣ ፕሮጀክቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በሳይንሳዊ ጥናት የተደገፈ የወንዝ ውሃ መውሰጃ ሥርዓት በማዘጋጀት በአካባቢው ዘላቂ፣ አስተማማኝና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

የአዋጭነት ጥናት፣ ዝርዝር ዲዛይንና ተግባራዊ ስልጠና የማንኛውም ዘላቂ የውሃ ፕሮጀክት ስኬት መሠረታዊ አካላት ናቸው። በመሆኑም ኢንስቲትዩቱ ይህንን ውል በከፍተኛ ሙያዊ ብቃት፣ በተፈለገው የጥራት ደረጃና በተቀመጠው የጊዜ ገደብ እንደሚያጠናቅቅ ሙሉ እምነት አለን። ሚኒስቴሩም የፕሮጀክቱ ስኬት እንዲረጋገጥ በሁሉም የአፈጻጸም ሂደቶች ተከታታይ ድጋፍ፣ ክትትልና ቅንጅት ያደርጋል" ሲሉ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም፣ ፕሮጀክቱ በተግባር ስልጠናዎች የቴክኒክ ባለሙያዎችን አቅም በማጠናከር፣ በውሃ ሀብት ልማት ዘርፍ ያለውን የሀገር ውስጥ የቴክኒክ አቅም ለማሳደግና ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን በተሻለ ብቃት ለማስፈጸም ጠቃሚ መሠረት እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታመነ ኃይሉ ሚኒስቴሩ ለኢንስቲትዩቱ የሚያደርገው ቀጣይና ጠንካራ ድጋፍ ተቋሙ አቅሙን እንዲያሳድግና እንዲጠናከር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ዶ/ር ታመነ እንዳሉት፣ ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ሥራዎችን በብቃት ያከናወነ በመሆኑ፣ በዚህም ውል መሠረት የተሰጠውን ኃላፊነት በባለቤትነት ስሜት፣ በተቆርቋሪነትና በሙያዊ ብቃት በመወጣት በተቀመጠው ጊዜና በሚፈለገው የጥራት ደረጃ ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የፕሮጀክቱ ዋና የሥራ ጊዜ 3 ወራት ሲሆን፣ የማጽደቅ ሂደቶችና የክፍያ መርሃ ግብሮች በሚጠይቁት ተጨማሪ ሂደት ምክንያት የኮንትራቱ ጊዜ በተጨማሪ 90 ቀናት እንደሚራዘም ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ በሱማሌ ክልል የሚገኙ ማህበረሰቦች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማሻሻል፣ የውሃ ምንጮችን በዘላቂነት ለማልማት፣ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ የውሃ አቅርቦት ሥርዓቶችን ለማስፋፋት እንዲሁም የአካባቢውን የቴክኒክ አቅም በተግባር ስልጠና ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።

Share this Post