በቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ/BaSRINET/ፕሮጀክት አማካኝነት በንግድና ስራ ፈጠራ ዙሪያ የተሰጠው ስልጠና የሴቶችን ተጠቃሚነት በሚገባ የሚያረጋግጥ ነው - ተሳታፊዎች

በቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ/BaSRINET/ፕሮጀክት አማካኝነት በንግድና ስራ ፈጠራ ዙሪያ የተሰጠው ስልጠና የሴቶችን ተጠቃሚነት በሚገባ የሚያረጋግጥ ነው - ተሳታፊዎች

ጎዴ፣ሰኔ 6/2018 ዓ.ም.(ው.ኢ.ሚ)በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ /BaSRINET/ፕሮጀክት አማካኝነት በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ በንግድና ስራ ፈጠራ ዙሪያ ለቀላፎ ወረዳ ሴቶች የተሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑ በስልጠናው ላይ በአጽንኦት ተገልጿል።

በጎዴ ከተማ ዋቢ ሸበሌ ቁጥር 2 ሆቴል ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ከቀላፎ ወረዳ የማህበረሰብ ክፍሎች የተወከሉ ሴቶችን አሳትፏል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የዋቢሸበሌ ባዘርኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ኢሊያስ ሁሴን እንዳመለከቱት ፕሮጀክቱ በአካባቢው አቅዶ ከሚተገብራቸው ቁልፍ ተግባራት መካከል የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት የሚገጥሙ ማህበራዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ዋናው ስራ ሲሆን በስራ ፈጠራና ክህሎት ላይ ተመርኩዞ የተዘጋጀው ይህ መድረክ የሴቶችን የኑሮ ሁኔታ ከግንዛቤ ያስገባና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ያለመ በመሆኑ ተሳታፊዎቹ በማህበርም ሆነ በግል ተደራጅተው ራሳቸውን እንዲለውጡ የሚያስችል መሆኑን አጠናክረው ተናግረዋል።

በተለይም እነዚህ ሴቶች ቋሚ ወርሃዊ ገቢ የሌላቸው ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ከስልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ ተግባር ላይ በማዋል በቀጣይ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ መሠማራት እንዲችሉ ትልቅ አቅም የፈጠረላቸውና በራስ መተማመናቸውን ያጎለበተ ነው ሲሉ አቶ ኢሊያስ ሁሴን ተናግረዋል።

ስልጠናውን የሰጡት በሶማሌ ክልል የስራና ክህሎት ፈጠራ ቢሮ የኢንተርፕራይዞች አቅም ግንባታ ቡድን መሪ አቶ ማሃድ ሙህመድ ሲሆኑ የስልጠናው አጀንዳዎች በዋናነት የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ራስን ስለማዘጋጀት፣ የስራ ፈጠራ ምንነትና ባህሪያት፣አስራ ሁለቱ የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የተቀረጹ አዋጪ የስራ ዘርፎችና ሴቶች ተጀራጅተው እንዲሰሩ መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች እንዲሁም የሚገጥሙ ተግዳሮቶችና የችግሮች መፍቻ መንገዶችን ባካተተ መልኩ የተቀረጹ ናቸው።

እንደ አቶ ማሃድ ገለጻ መድረኩ ከፍተኛ የሰልጣኞች መነቃቃትና ተነሳሽነት የተስተዋለበት እንደነበረ አመልክተው ተሳታፊዎች ወደ ተግባር ለመግባት ያዳግተናል በማለት የጠቀሷቸው የጎርፍ መከሰት ችግር፣የፋይናንስ እጥረት፣የገበያ ሰንሰለት የማግኘት ውስንነት እንዲሁም ሌሎች ተፈጥሯዊና ሰው -ሰራሽ ክስተቶች እንደሆኑ አመልክተው እነዚህ ጉዳዮች ትኩረት የሚሹ በመሆናቸው በሚመለከተው አካል እንዲፈቱ ድጋፍና ክትትል ቢደረግ እነዚህ ሴቶች ለለውጥ ጊዜ የማይፈጅባቸው መሆናቸውን ማስተዋል ችያለሁ ብለዋል።

አያይዘውም የማህበረሰቡ ግማሽ አካል የሆኑትን ሴቶች ለማብቃትና ስራ ፈጥረው ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ለማድረግ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል የሚሰራው ስራ ሊያስመሰግን የሚገባው ሰናይ ተግባር በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ሲሉም አሳስበዋል።

የቀላፎ ወረዳ የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ ወ/ሮ አስራ ማህመድ በስልጠናው ላይ የተገኙ ሲሆን በወረዳው ገቢያቸው አናሳ የሆኑት ሴቶች በአቅም ግንባታ ስልጠናው እንዲሳተፉ መደረጋቸው መልካም አጋጣሚ በመሆኑ አመስግነው ነዋሪዎቹ ወደ ፊት ስራ ፈጥረው ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንሰራለን ብለዋል።

በስልጠናው ላይ የተሳተፉት የቀላፎ ወረዳ ነዋሪ ወ/ሮ ፍርሃን ሙሃመድ በበኩላቸው ስልጠናው በርካታ ግንዛቤ የጨበጡበትና የግልና የአካባቢውን ችግር ሊፈታ በሚችል የስራ ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችል ውስጣዊ ተነሳሽነት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።

አብዛኞቹ ተሳታፊዎች የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት ላመቻቸው የስልጠና መድረክና ለተደረገው ድጋፍ በእጅጉ ምስጋና አቅርበው በቀጣይም ወደስራ ለመግባት የሚያስችሉ ተጨማሪ እገዛዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

Share this Post