ከ88 ሺ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የሾኔ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመረቀ።
ከ88 ሺ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የሾኔ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመረቀ።
ግንቦት 18/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጋር በመተባበር በሀድያ ዞን ያስገነባው የሾኔ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ፕሮጀክቱ 88 ሺ 658 የሚጠጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ዶ/ር እንደሻው ጣሰው በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ፕሮጀክቱን በይፋ ከፍተዋል። በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ፕሮጀክቱ ለቀጣዮቹ 20 ዓመታት የሾኔ ከተማን ነዋሪዎች በበቂ ሁኔታ የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
“ውሃ ህይወት ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የተገነባውን ሀብት መጠበቅ፣ መንከባከብና በአግባቡ መጠቀም የህብረተሰቡ ኃላፊነት መሆኑን አሳስበዋል።
መንግስት ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማፋጠን በርካታ ልማታዊ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የጠቀሱት ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ ህብረተሰቡም በሀገር ግንባታ የራሱን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ገልፀዋል።
ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ አስተዋፅኦ ላደረጉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮች፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ኃላፊዎች እንዲሁም ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል።
የሾኔ ከተማ አስተዳደር ኃላፊ አቶ አበራ በዶሬ በበኩላቸው፣ ከተማዋ በለውጡ መንግስት ዘመን ከፍተኛ የልማት እድገት ላይ መሆኗን ገልፀው፣ የዛሬውን የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ጨምሮ በርካታ ማሳያ ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን አስታውቀዋል።
ፕሮጀክቱ የከተማውን የመጠጥ ውሃ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ እንደሚያሟላም ነው ኃላፊው የገለጹት።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ልማት ፈንድ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዶጊሶ ጎና እንደገለፁት፣ ፕሮጀክቱ የባስኬት ፈንድ ፕሮጀክት አካል ሲሆን የፋይናንስ ድጋፉ ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ ከጣሊያን ልማት ድርጅት እና ከፈረንሳይ ልማት ድርጅት የተገኘ ሲሆን፣ ከ383 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ለ20 ዓመታት በበቂ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጥ ታቅዶ የተገነባ ሲሆን፣ 60 በመቶ ወጪው በረጅም ጊዜ ብድር በአነስተኛ ወለድ በሚኒስቴሩ የተሸፈነ ሲሆን ቀሪው 40 በመቶ ደግሞ በክልሉ መንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ መሸፈኑን ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ አራት የውሃ ጉድጓዶች እና ሁለት 800 ሜትር ኪዩብ ሪዘርቫየሮች የተገነቡ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ከነበሩት 12 የውሃ ቦኖዎች በተጨማሪ 5 አዳዲስ ቦኖዎች ተገንብተዋል ብለዋል።
በተጨማሪም የፕሮጀክቱን ዘላቂነት ለማረጋገጥ የጥገናና የመለዋወጫ ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን አቶ ዶጊሶ ገልጸዋል።
የአገልግሎት አሰጣጡን ለመቆጣጠር በከንቲባው የሚመራ ቦርድ መቋቋሙን የገለፁት አቶ ዶጊሶ፣ ቦርዱ በየሶስት ወሩ የፕሮጀክቱን አፈፃፀም በመገምገም አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ አስታውቀዋል።
የውሃ ምንጮችን በመጠበቅና በአካባቢው ዛፎችን በመትከል የውሃ መጠን እንዳይቀንስ መንከባከብ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በተጨማሪም የተወሰደው ብድር በ20 ዓመታት ውስጥ እንዲመለስ የውሃ ታሪፍ ማሻሻያ እና የአገልግሎት ጥራት ማሻሻል እንደሚያስፈልግም ነው አቶ ዶጊሶ የገለጹት።
በምረቃ ሰነስርዓቱ ላይ የክልል ከፍተኛ ሀላፊዎች ፣የሚኒስቴሩ የስራ ሀላፊና የዘርፉ ሙያተኞች የዞንና የወረዳ ከፍተኛ ሀላፊዎች እንዲሁም ነሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።