በ6.2 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው የአዳማ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በይፋ ተመረቀ።
በ6.2 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው የአዳማ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በይፋ ተመረቀ።
አዳማ፣ ሰኔ 30/ 2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) ከ1.1 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍልን ተጠቃሚ የሚያደርገውና በ6.2 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው የአዳማ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ዛሬ በይፋ ተመርቆ ወደ አገልግሎት ገብቷል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ማኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ፕሮጀክቱ ከንድፍ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ በርካታ የምህንድስና፣ የፋይናንስ፣ የአስተዳደርና የዓለም አቀፍ ፈተናዎችን በማለፍ የተጠናቀቀ ሀገራዊ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፣ ፕሮጀክቱ 1.2 ሜትር ዲያሜትር ያለው ግዙፍ የውሃ ማስተላለፊያ (Transmission Main) ቧንቧ በመጠቀም የተገነባ ሲሆን፣ ይህን ያክል መጠን ያለውን ቧንቧ ከውጭ ሀገር ማስመጣት፣ በሥራ ቦታ ማንቀሳቀስና መግጠም ከፍተኛ የምህንድስና ብቃትና ጥንቃቄ የጠየቀ ሥራ ነበር ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በተያዘለት የአምስት ዓመት ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ የዲዛይን ክለሳና የውሃ ምንጭ ልማት ሥራዎች በትይዩ መከናወናቸውን የገለጹት ክቡር አምባሳደሩ በሂደቱም የመጀመሪያው አማካሪ ድርጅት ባሳየው ደካማ አፈጻጸም ምክንያት ውሉ መቋረጡን አስታውሰዋል።
ይህ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ሊቆም የሚችልበት አደገኛ ወቅት ላይ የነበረ ቢሆንም፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ፣ የአዳማ ከተማ አስተዳደርና የውሃ አገልግሎት ተቋም በጋራ በመተባበር ጊዜያዊ የባለሙያዎች ቡድን በማቋቋም የኮንትራት አስተዳደርና የዲዛይን ክለሳውን በራሳቸው አቅም በመምራት ፕሮጀክቱ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ይህም የቀውስ አስተዳደርና የአመራር ብቃት የፕሮጀክቱን ህልውና ያዳነ ወሳኝ እርምጃ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እንደ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፣ ፕሮጀክቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የዓለም አቀፍ የካርጎ መስተጓጎል፣ የጸጥታ ችግሮችና ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ያስከተሉትን ፈተናዎች ተቋቁሞ ማለፉን ጠቅሰው፣ መንግሥት ከውጭ የሚገቡ የፕሮጀክት ዕቃዎችን የቀረጥ ነፃ መብት በመስጠት እና የኮንትራት ማሻሻያዎችን በወቅቱ በማድረግ ፕሮጀክቱ እንዳይስተጓጎል መደረጉን አስረድተዋል።
በፕሮጀክቱ 15 እስከ 600 ሜትር ጥልቀት ያላቸው የጥልቅ ጉድጓዶች ፣ 10 ግዙፍ የውሃ ማጠራቀሚያዎች፣ 245 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የውሃ ማስተላለፊያና ስርጭት መስመር፣ የኤሌክትሮ-መካኒካል ሥራዎች፣ ዘመናዊ የSCADA የውሃ አስተዳደር ሥርዓት፣ ባለ አምስት ወለል (G+5) የቢሮ ሕንፃ እና 14 የገጠር ውሃ ማደያዎች መገንባታቸውንም አክለው ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ ጠቅላላ ወጪ 1.5 ቢሊየን ብር፣ 69.7 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እና 1.3 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ብር ሲተመን 6.2 ቢሊየን ብር መሆኑንና ከዚህም ውስጥ 49.1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በአፍሪካ ልማት ባንክ ብድር የተሸፈነ መሆኑን ክቡር አምባሳደሩ ተናግረዋል።
አክለውም በአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍ ከተከናወኑ አራት የከተማ ውሃ ፕሮጀክቶች ውስጥ የጎዴና የቢቸና ፕሮጀክቶች ቀደም ብለው ወደ አገልግሎት የገቡ ሲሆን የመቀሌ ፕሮጀክት ደግሞ እስከ ታህሳስ 2019 ዓ.ም. ተጠናቆ ወደ አገልግሎት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ የአዳማ ከተማን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በማሻሻል እናቶችን ከውሃ ፍለጋ እንግልት እንደሚያድን፣ የሕዝብ ጤናን እንደሚያሻሽል፣ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን እንደሚያበረታታ እና የከተማዋን ኢኮኖሚ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
በመጨረሻም ክቡር አምባሳደሩ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የውሃ መስመሮችና የኤሌክትሪክ ኬብሎች ከተለያየ ጉዳት እንዲጠበቁ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች፣ የጸጥታ አካላትና የአካባቢው አስተዳደር የባለቤትነት ስሜት በመውሰድ ንብረቱን እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚሁ አጋጣሚም ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን አስተዋጽኦ ላበረከቱት ለአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር፣ ለኦሮሚያ ክልል መንግሥት፣ ለአዳማ ከተማ አስተዳደር፣ ለአዳማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት፣ ለውሃ ልማት ፈንድ፣ ለዋና ተቋራጩ CGCOC Group፣ ለአማካሪው እንዲሁም ለሁሉም አመራሮችና ባለሙያዎች ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ፣ የኦሮሚያ ክልል አመራሮች፣ የአዳማ ከተማ አስተዳደር፣ የኦሮሚያ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የCGCOC Group ተወካዮች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ኮንትራክተሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።