በ405 ሚሊዮን ዶላር የሚተገበረው የHCO ፕሮጀክት በ65 ወረዳዎች ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ ነው ተባለ።
በ405 ሚሊዮን ዶላር የሚተገበረው የHCO ፕሮጀክት በ65 ወረዳዎች ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ ነው ተባለ።
አዳማ፣ ሰኔ 4/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ)
በ405 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በኢትዮጵያ መንግሥትና በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚተገበረው Human Capital Operation (HCO) ፕሮጀክት በሀገሪቱ 65 ወረዳዎች የውሃ፣ የጤና፣ የትምህርት ፣ የኢነርጂ ፣ የግብርናና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አገልግሎቶችን በማስፋፋት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ተጨባጭ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑ ተገለጸ።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የHuman Capital Operation ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሀብተሙ ዱጉማ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ በስተቀር በሁሉም ክልሎች በሚገኙ 65 ወረዳዎች ላይ እየተተገበረ ሲሆን፣ በተለይም የሰው ሀብት ልማት ዝቅተኛ በሆነባቸው፣ በድርቅ ተጽዕኖ በሚደርስባቸው፣ በድንበር አካባቢዎች እና ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ለሚገኙ ዜጎች የውሃ፣ የሳኒቴሽንና የኢነርጂ አገልግሎቶችን በጤና፣ በትምህርት እና በማህበረሰብ ተቋማት ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።
በ405 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በኢትዮጵያ መንግሥትና በWorld Bank ድጋፍ ለአምስት ዓመታት የሚተገበረው ፕሮጀክት ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ትግበራ መግባቱንም አስተባባሪው ገልጸዋል።
በውሃ፣ ሳኒቴሽንና ንፅህና (WASH) ዘርፍ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ማሳደግ፣ የሳኒቴሽን አገልግሎቶችን ማሻሻል እና የግልና የአካባቢ ንፅህናን ማጠናከር የፕሮጀክቱ ቁልፍ ትኩረቶች ሲሆኑ፣ በትምህርትና በጤና ተቋማት ውስጥም በርካታ የውሃና ንፅህና ተያያዥ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ከግብርና ጋር በተያያዘ የምግብ ዋስትናና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን በማሳደግ የቤተሰብ ኑሮን የሚያሻሽሉ የግብርና ስራዎችን ማጠናከር የፕሮጀክቱ የትኩረት መስክ ነው ብለዋል።
በኢነርጂ ዘርፍ ደግሞ የታዳሽ ኃይል ልማትን ለማስፋፋት፣ ንጹህ የማብሰያ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ እና የፀሐይ፣ የባዮጋዝና ሌሎች ታዳሽ ኃይል ምንጮችን በማበረታታት የኃይል ተደራሽነትን ለማሳደግ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አኳያም ፕሮጀክቱ የሚያተኩረው የሴቶችን፣ የሕፃናትን እና ሌሎች ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ጤናማ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ምርታማ ማህበረሰብ መፍጠር ላይ ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ HCO ፕሮጀክት በውሃ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢነርጂ፣ በግብርና፣ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይና በተቋማት አቅም ግንባታ መስኮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየተተገበረ መሆኑን አቶ ሀብታሙ ገልጸዋል።
አቶ ሀብተሙ እንዳሉት፣ ፕሮጀክቱ የተቋማት አቅም ግንባታን ከዋና ዋና ትኩረቶቹ መካከል በማድረግ በተለያዩ ዘርፎች ስልጠናዎችን እየሰጠ ሲሆን፣ በታዳሽ ኃይል ልማትና ቴክኖሎጂዎች ላይ ለክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮዎች የHCO አስተባባሪዎች እና ለኢነርጂ ልማት ዳይሬክተሮች የሚሰጠው የአሰልጣኞች ስልጠና የዚህ ጥረት አካል መሆኑን ገልጸዋል።
አስተባባሪው በማጠቃለያቸው፣ የHCO ፕሮጀክት ጤናማ፣ የተማረ፣ ምርታማ እና ተጠቃሚ ማህበረሰብ በመፍጠር የሀገሪቱን የሰው ኃይል ልማት ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል፣ የውሃ ፕሮጀክቶች ዘላቂነት እንዲረጋገጥ ተጠቃሚው ማህበረሰብ ፕሮጀክቶችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብ፣ ውሃን በቁጠባ በመጠቀም እና በጊዜው ጥገና በማድረግ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ስልጠና የወሰዱ ባለሙያዎችም በየአካባቢያቸው በመውረድ ለማህበረሰቡ፣ ለትምህርት ቤቶች እና ለጤና ተቋማት ዕውቀቱን በማስተላለፍ ንጹህ ውሃና ንጹህ ኢነርጂ ተደራሽ እንዲሆን ፣ ጤናማና አምራች ዜጋ እንዲስፋፋ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።