በ312.2 ሚሊዮን ብር የጉራድሃሞሌ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የቧንቧና መገጣጠሚያ አቅርቦት ውል ተፈረመ፡፡
በ312.2 ሚሊዮን ብር የጉራድሃሞሌ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የቧንቧና መገጣጠሚያ አቅርቦት ውል ተፈረመ፡፡
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ.)
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሱማሌ ክልል የሚገነባውን የጉራድሃሞሌ የአየር ንብረትን የሚቋቋም ባለብዙ መንደር የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት ትግበራን ለማፋጠን የHDPE ቧንቧዎች (ሎት-1) እና የCast Iron እና HDPE መገጣጠሚያዎች (ሎት-2) አቅርቦት ውል ከሹምቡሮ ፕላስቲክ ፋብሪካ ጋር ተፈራርሟል።
ውሉ በዋን ዋሽ ፕሮግራም (One WaSH National Program) በጀት የሚተገበር ሲሆን፣ ጠቅላላ ወጪው 312,224,803.35 (ሦስት መቶ አስራ ሁለት ሚሊዮን ሁለት መቶ ሃያ አራት ሺህ ስምንት መቶ ሶስት ብር ከ35 ሳንቲም) ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ 32,891 ዜጎችንና 28,933 እንስሳትን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል።
የውል ስምምነቱን የተፈራረሙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ፣ ፕሮጀክቱ በአካባቢው የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን በማሻሻል የሕብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ከፍ ከማድረጉም ባሻገር፣ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የውሃ አቅርቦት ሥርዓት በመገንባት ዘላቂ ልማትን እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ክቡር አምባሳደሩ አክለውም፣ የፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ በአስቸኳይ እየተከናወነ በመሆኑ የቧንቧና የመገጣጠሚያ እቃዎች በውሉ መሠረት በተያዘው ጊዜ መቅረባቸው ለፕሮጀክቱ ስኬት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፣ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ እቃዎች በ40 ቀናት፣ ከውጭ የሚገቡት ደግሞ በ60 ቀናት ውስጥ በማቅረብ የተገባው ቃል እንዲከበር አሳስበዋል።
እንደ ክቡር አምባሳደሩ ገለጻ፣ የመጠጥ ውሃ ልማት ፕሮጀክቶች በወቅቱ ሲጠናቀቁ የሕብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ከማሻሻል ባሻገር የጤና፣ የትምህርት፣ የኢኮኖሚና የአካባቢ ጥበቃ ጥቅሞችን ያመጣሉ። ስለዚህ ጥራት፣ ፍጥነትና ተጠያቂነት በሁሉም የሥራ ሂደቶች የማይነጣጠሉ መርሆዎች መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም፣ መንግሥት ለውሃ አቅርቦት መሠረተ ልማቶች ትልቅ ትኩረት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት ተቋራጩ ውሉን በጥራትና በተያዘው ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚጠበቅበት በመግለጽ ሚኒስቴሩም ለፕሮጀክቱ ስኬታማ አፈጻጸም አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
ክቡር አምባሳደሩ እንዳሉት፣ ሹምቡሮ ፕላስቲክ ፋብሪካ ከዚህ ቀደም ከሚኒስቴሩ ጋር የሠራቸውን ፕሮጀክቶች በታማኝነት፣ በጥራትና በወቅቱ በማጠናቀቁ መልካም ተሞክሮ ያለው በመሆኑ፣ ይህንንም ውል በተመሳሳይ ብቃት እንደሚፈጽም ሙሉ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የሹምቡሮ ፕላስቲክ ፋብሪካ ሥራ አስፈጻሚ (CEO) አቶ አፈትሒ አህመድ በበኩላቸው ድርጅታቸውን በድጋሚ በማመን ውሉን ስለሰጠ ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ምስጋና አቅርበው፣ በውሉ የተቀመጡትን የጥራት፣ የጊዜና የቴክኒክ መስፈርቶች በሙሉ በማሟላት እቃዎቹን በወቅቱ በማቅረብ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
የጉራድሃሞሌ የአየር ንብረትን የሚቋቋም ባለብዙ መንደር የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት በሱማሌ ክልል የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን በማሳደግ፣ የአካባቢውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማፋጠን እየተተገበሩ ካሉ ቁልፍ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው።