በ2019 በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የተገኙ ስኬቶችን እናጠናክራለን፤ ያሉ ክፍተቶችንም እንሞላለን" ሲሉ ክቡር ዶ/ር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ ገለጹ።

በ2019 በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የተገኙ ስኬቶችን እናጠናክራለን፤ ያሉ ክፍተቶችንም እንሞላለን" ሲሉ ክቡር ዶ/ር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ ገለጹ።

ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ)

ክቡር ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት፣ ከክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮዎች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የ2018 በጀት ዓመት የዘርፉ አፈጻጸም ግምገማና ለ2019 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ በተዘጋጀ አገራዊ የውይይት መድረክ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።

ክቡር ሚኒስትሩ በንግግራቸው የ2018 በጀት ዓመት የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ አፈጻጸም ከፌዴራልና ከሁሉም ክልሎች ከተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በመገምገም፣ በዓመቱ የተመዘገቡ ውጤቶችን፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንና ለቀጣዩ በጀት ዓመት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በጥልቀት የሚመክር መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም፣ ባለፉት አምስት ቀናት ከሚኒስቴሩ አመራሮች፣ ከማኔጅመንት እና ከመላው ሠራተኞች ጋር የተካሄዱ የውስጥ ግምገማዎች የተቋሙን የስትራቴጂክ ዕቅዶች አፈጻጸም፣ የሪፎርም ሥራዎች፣ የተቋማዊ አሠራሮችና የአገልግሎት አሰጣጥ በሰፊው እንደተገመገሙ ገልጸዋል።

እንዲሁም በመላ ሀገሪቱ እየተተገበሩ ያሉ የውሃና ኢነርጂ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በዝርዝር መገምገሙን ጠቅሰው፣ የፕሮጀክቶችን ፍጥነት፣ ጥራት፣ የበጀት አጠቃቀም፣ የኮንትራት አስተዳደርና ለህዝብ የሚያስገኙትን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ የማሻሻያ እርምጃዎች መለየታቸውን አብራርተዋል።

ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም፣ በግምገማዎቹ የተገኙ ጠንካራ አፈጻጸሞችን በማጠናከር፣ የታዩ ክፍተቶችን በአጭር ጊዜ በመሙላት፣ የተቋማት ቅንጅትን በማሳደግ፣ የፕሮጀክት ክትትልና ግምገማን በማጠናከር እና ለህዝብ የሚሰጡ የውሃና ኢነርጂ አገልግሎቶችን የበለጠ ተደራሽ፣ ፍትሃዊና ውጤታማ ለማድረግ በ2019 በጀት ዓመት ትኩረት የሚሰጣቸው ቅድሚያ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ገልጸዋል።

በዛሬው የውይይት መድረክ ከክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮዎች፣ ከተጠሪ ተቋማት እና ከአጋር አካላት ጋር በ2018 በጀት ዓመት በውሃ ሀብት አስተዳደር፣ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን፣ በኢነርጂ ተደራሽነት ከአደጋ ሰጋት መከላከል፣ ከሪፎርም አተገባበር ፣ ከአገልግሎት አሰጣጥና በሌሎች ተያያዥ የዘርፉ አፈጻጸሞች ላይ ሪፖርቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

በመጨረሻም ክቡር ሚኒስትሩ በመድረኩ የተገኙ የፌዴራልና የክልል አመራሮች፣ የተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለተሳትፎአቸው ምስጋና አቅርበዋል።

በመድረኩ የውሃ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች እና አካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት አመራሮች፣ የክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በስፋት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

Share this Post