የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሠ ምድር ውሃ የአየር ንብረት መቋቋም ፕሮጀክት የ2018 ዓ.ም. የአፈጻጸም ሪፖርት መድረክ ተጠናቀቀ።

የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሠ ምድር ውሃ የአየር ንብረት መቋቋም ፕሮጀክት የ2018 ዓ.ም. የአፈጻጸም ሪፖርት መድረክ ተጠናቀቀ።

ሐምሌ 14/2018 ዓ.ም.የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሠ ምድር ውሃ የአየር ንብረት መቋቋም ፕሮጀክት (Horn of Africa Groundwater for Resilience Project) የ2018 ዓ.ም. የአፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ መድረክ ተካሂዶ በተሳታፊዎች የተለያዩ ግብዓቶች የቀረቡበትና ለተነሱ ጉዳዮች ምላሽ የተሰጠበት ሆኗል።

በመድረኩ የፕሮጀክቱ አማካሪዎችና ኮንሰልታንቶች የ2018 ዓ.ም. የአፈጻጸም ሪፖርትን ያቀረቡ ሲሆን፣ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ፣ የአፈጻጸም ሂደት፣ የትግበራ አካባቢዎች፣ እንዲሁም በትግበራው ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በስፋት አቅርበዋል።

በተለይም በአንዳንድ የፕሮጀክቱ ትግበራ አካባቢዎች የሚታዩ የጸጥታና ደህንነት ችግሮች፣ በቂ የነዳጅ አቅርቦት አለመኖር፣ እንዲሁም የመንገድ ሁኔታ አመቺ አለመሆን የፕሮጀክቱን አፈጻጸም እያስተጓጎሉ ያሉ ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አንዳንድ ኮንትራክተሮች የነዳጅ እጥረትን በአማራጭ ዘዴዎች በመቋቋም፣ የትራንስፖርት ችግሮችንም በአማራጭ መንገዶች በመፍታት የፕሮጀክቱ ሥራ እንዳይስተጓጎል የወሰዷቸውን የመፍትሔ እርምጃዎች አብራርተዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ የቀረበው ሀሳብ እንደሚያሳየው፣ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያና ጅቡቲ የሚተገበር በመሆኑ በአንድ ሀገር የሚከሰቱ ችግሮች በሌሎች አገራትም ተጽእኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ተጠቁሟል። በመሆኑም የውሃ ችግር ተጎጂ የሆኑ ማኅበረሰቦች በወቅቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ኮንትራክተሮች ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርጉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አሳስቧል።

እንዲሁም በግዢ ሂደትና በጥናት ሥራዎች ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ለዚህ ፕሮጀክት ትግበራ አማካሪዎች ስራ ሰርተው ገቢ እንዲያገኙ ጥሪ መደረጉም እድለኛነት መሆኑንና በዚህ ዕድል ተጠቃሚ የሆኑ አማካሪዎችም በሙሉ ሀላፊነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

የነዳጅ ችግርን ለመቅረፍም ሌሎች አማራጮችን መጠቀም እንዳለባቸው ተመልክቷል ።

በአጠቃላይ መድረኩ በርካታ ልምዶች የተቀሰሙበት እንደነበረና ለቀጣይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም የተቃና ስራ ለማከናወን የሚያስችል ግብዓት የተወሰደበት ነው።

Share this Post