በቀጣዮቹ አራት ዓመታት 100 በመቶ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማሳካት አዲስ የውሃና ሳኒቴሽን አስተዳደር ሞዴል ለውይይት ቀረበ።

በቀጣዮቹ አራት ዓመታት 100 በመቶ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማሳካት አዲስ የውሃና ሳኒቴሽን አስተዳደር ሞዴል ለውይይት ቀረበ።

አዳማ፣ ሰኔ 24/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) መንግሥት በቀጣዮቹ አራት ዓመታት 100 በመቶ የኢትዮጵያን ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ መሆኑን የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ገለጹ።

ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ይህን የገለጹት በአዳማ ናፍሌት ሆቴል በተካሄደው የ"የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የሳኒቴሽን ሥርዓት አስተዳደር ሞዴል (Water Supply and Sanitation System Management Model)" ረቂቅ ላይ በተዘጋጀ የሁለት ቀናት አውደ ጥናት መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ነው።

በንግግራቸው እንደገለጹት፣ መንግሥት ከልማት አጋሮችና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በገጠርና በከተማ ከ230 ሺህ በላይ የውሃ ተቋማትን በመገንባት ከ82 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

ሆኖም አሁንም ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን የሚገመቱ ዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ አለመሆናቸውን ጠቅሰው ይህንን ክፍተት ለመሙላት የተቀናጀ ስትራቴጂና የተጠናከረ የትግበራ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ክቡር አምባሳደሩ ገለጻ በውሃ ፕሮጀክቶች ዕቅድ፣ ግንባታና አስተዳደር ሂደት የአየር ንብረት ለውጥ፣ የውሃ ምንጮች መቀነስ፣ የፋይናንስ እጥረት፣ ፈጣን የህዝብ ቁጥር እድገት፣ የኃይልና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ተግዳሮቶች እያጋጠሙ መሆናቸውን ጠቁመው፣ እነዚህን ፈተናዎች ያገናዘበ በፖሊሲ የተደገፈና ዘላቂ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የውሃ ተቋማት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ የአጋር አካላትን ተሳትፎ ማጠናከር፣ አማራጭ የኃይል ምንጮችን በተለይም የፀሐይ ኃይልን መጠቀም፣ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ ትብብር ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ክቡር አምባሳደሩ አክለውም፣ የመንግሥት ትኩረት የውሃ ተቋማትን መገንባት ብቻ ሳይሆን ለተጠቃሚው ዘላቂ፣ ፍትሃዊና ጥራት ያለው የመጠጥ ውሃና የሳኒቴሽን አገልግሎት ማቅረብ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የተዘጋጀው የአስተዳደር ሞዴል የውሃ ተቋማትን በወቅቱ የመጠገን አቅም ማሳደግ፣ የውሃ ጥራትን በተከታታይ መከታተል፣ የአገልግሎት ተጠያቂነትን ማጠናከር፣ የማህበረሰብና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን ማሳደግ እንዲሁም የውሃ አገልግሎት ተቋማትን በፋይናንስና በተቋማዊ አቅም ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑንም አብራርተዋል።

የአውደ ጥናቱ ዓላማም በውሃ አቅርቦትና በሳኒቴሽን ዘርፍ ያሉ ችግሮችን፣ መልካም ተሞክሮዎችንና የመፍትሔ ሀሳቦችን በስፋት በመወያየት የጋራ መግባባት በመፍጠር የሥርዓቱን ውጤታማነትና ዘላቂነት ማሳደግ መሆኑን አክለው ገልጸዋል ።

በአውደ ጥናቱ የገጠር መጠጥ ውሃ ተቋማት አስተዳደር፣ ከፕሮጀክት ዝግጅት እስከ አገልግሎት አሰጣጥ ድረስ ያሉ ችግሮችና የመፍትሔ አማራጮች የቀረቡ ሲሆን፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የሳኒቴሽን ሥርዓት አስተዳደር ሞዴል ረቂቅም ለውይይት ቀርቧል።

በውይይቱ የፌዴራልና የክልል ውሃና ኢነርጂ ተቋማት ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች፣ የውሃ አገልግሎት ተቋማት፣ የልማት አጋሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የሁለት ቀን አውደ ጥናቱም በቀጣዩ ቀን በቴክኒካል ውይይቶችና የማጠቃለያ ምክረ ሀሳቦች እንደሚቀጥል ተገልጿል።

Share this Post