የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት 100 ዘመናዊ የአየር ሁኔታ ጣቢያዎችን ለመትከል የግዥ ውል ፈረመ።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት 100 ዘመናዊ የአየር ሁኔታ ጣቢያዎችን ለመትከል የግዥ ውል ፈረመ።
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት ማዕቀፍ 100 ዘመናዊ አውቶማቲክ የአየር ሁኔታ መመዝገቢያ ጣቢያዎችን (AWS) ለመግዛት ከጣሊያኑ SIAP+MICROS S.P.A ድርጅት ጋር የግዥ ውል መፈራረሙ ተገለጸ።
በውል ስምምነቱ ወቅት የኢንስቲትዩቱ የትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሳምነው ተሾመ እንደገለጹት፣ ጣቢያዎቹ በጎርፍ መከላከል ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው የአዋሽ፣ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች እና የኦሞ–ጊቤ ተፋሰሶች አካባቢዎች ላይ እንደሚተከሉ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የSIAP+MICROS S.P.A የቢዝነስ ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ማሪዮ ሞንታሪዮ ድርጅታቸው ዘመናዊ ጣቢያዎቹን በአራት ወራት ውስጥ ለማስረከብ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአዋሽ፣ በስምጥ ሸለቆ ሐይቆች እና በኦሞ–ጊቤ ተፋሰሶች 100 አውቶማቲክ የአየር ሁኔታ ጣቢያዎችን መትከል የአየር ሁኔታና የውሃ ሀብት መረጃ ሽፋንን በማሳደግ በተለይም ለጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተመላክቷል።
ጣቢያዎቹ የዝናብ፣ የሙቀት፣ የንፋስ እና የአየር እርጥበት መረጃዎችን በቀጣይነት በመሰብሰብ የተሻለ የአየር ሁኔታ ትንበያ ለማዘጋጀት እንደሚያስችሉ ተገልጿል።
በተጨማሪም በጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትን በማጠናከር የድርቅ፣ የጎርፍ እና ሌሎች ከፍተኛ የአየር ጠባይ ክስተቶችን አስቀድሞ ለመለየት ወሳኝ መረጃ ያቀርባሉም ነው የተባለው።
ከዚህ ባሻገር ጣቢያዎቹ ለመስኖ እርሻ፣ ለውሃ ሀብት አስተዳደር እና ለግብርና ውሳኔዎች ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም የረጅም ጊዜ የአየር ንብረት ጥናቶችን ለማገዝ እንደሚያስችሉ ተጠቁሟል።
ፕሮጀክቱ የሜትሮሎጂ፣ የውሃ ሀብት እና የአደጋ ስጋት አስተዳደር ተቋማትን የመረጃ ማሰባሰብና የትንተና አቅም በማጠናከር ተቋማዊ አቅም ግንባታን እንደሚያበረታታ ተገልጿል።
በተጨማሪም የቴክኒክ ባለሙያዎችን በጣቢያዎቹ ተከላ፣ ጥገና እና የመረጃ አስተዳደር ዙሪያ ለማሰልጠን እንዲሁም በተቋማት መካከል የመረጃ ልውውጥና ቅንጅትን ለማጠናከር ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።
በአጠቃላይ የአየር ሁኔታ ጣቢያዎቹ መተከል የጎርፍ አደጋ ቅነሳን፣ የውሃ ሀብት አስተዳደርን፣ የግብርና ምርታማነትን እና የሀገሪቱን የአየር ሁኔታ ክትትልና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያጠናክር ተገልጿል።