በ10 ከተሞች የሚገኙ የሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ተገመገመ

በ10 ከተሞች የሚገኙ የሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ተገመገመ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 07 ቀን 2019 ዓ.ም

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በ10 ከተሞች በሁለተኛው የከተማ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት (SUWSSP) ሥር እየተገነቡ ያሉ 11 የሳኒቴሽን ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ገመገመ።

የግምገማው ዓላማ ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸውን ፕሮጀክቶች ለይቶ በመወያየት ችግሮችን መፍታትና ሥራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ ነው።

የውሃ ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ኢንጅነር አክሊሉ አዳኜ በመድረኩ ላይ በመገኘት፣ ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት ተጠናቀው ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውሉ የተለዩ ችግሮችን በቅንጅት መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በግምገማው የፋይናንስ እጥረት፣ የሰው ኃይልና የመሣሪያ እጥረት፣ የግንባታ ግብዓቶች መዘግየት፣ ደካማ የሥራ ዕቅድ፣ የመሬት ካሳና የጸጥታ ችግሮች ለፕሮጀክቶቹ መዘግየት ከሚያደርሱ ማነቆዎች መካከል ተጠቅሰዋል።

ሚኒስቴሩ ከክልል ውሃ ቢሮዎች፣ ከከተማ ውሃ አገልግሎት ተቋማት፣ ከተቋራጮችና ከአማካሪዎች ጋር ቅንጅትን በማጠናከር ማነቆዎቹን ለመፍታትና ፕሮጀክቶቹን በወቅቱ ለማጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን ገልጿል።

ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ ለሕዝብ ጤና መሻሻል፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለዘላቂ የከተማ ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ተብሏል።

Share this Post