የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአራተኛ ዙር ከተለዩ 10 ሶላር አስመጪ አዳዲስ ድርጅቶች ጋር የስምምነት ውል ተፈርሟል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአራተኛ ዙር ከተለዩ 10 ሶላር አስመጪ አዳዲስ ድርጅቶች ጋር የስምምነት ውል ተፈርሟል።

ሰኔ 2/2018 ዓም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በውጤት ተኮር የገንዘብ ድጎማ (Result Based Finance) በጣም ገጠራማ በሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የቤት ውስጥ ሶላር ቴክኖሎጂዎችን ለማሰራጨት ውል ከገቡ ድርጅቶች ጋር የአፈጻጸም ግምገማ እና የጋራ አቅጣጫ ማስቀመጫ ውይይት በማካሄድ በአራተኛ ዙር ከተለዩ 10 አዳዲስ ድርጅቶች ጋር የስምምነት ውል ተፈራርሟል።

የውል ስምምነቱን የፈረሙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ደ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ትግበራን በዋናነት እየመራና እያስተባበረ የሚገኝ መሆኑን ገልጸው በአሁኑ ወቅት ከዓለም ባንክ በተገኘ የፋይናንስ ድጋፍ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም (ELEAP) እና የገጠር ኤሌክትሪክና መብራት ተደራሽነት ፕሮጀክት (ADELE) በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከእነዚህ መርሃ-ግብሮች መካከል አንዱ የሆነው የADELE ፕሮጀክት፤ በሶላር ሚኒ ግሪድ፣ በቤት ውስጥ ሶላር ሲስተም (Solar Home System) እና በተቋማዊ ሶላር ሲስተም ቴክኖሎጂዎች የህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በጣም ገጠራማ ለሆኑና ተደራሽነቱ አስቸጋሪ ለሆነባቸው አካባቢዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት የውጤት ተኮር የገንዘብ ድጎማ (RBF) የተመቻቸ ሲሆን፥ ለዚህም ወደ 14 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት ተመድቦ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአማካሪ ድርጅቶች ጋር በመሆን የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል፡፡

በፕሮጀክቱ የአፈጻጸም እቅድ መሰረት በተቀመጡ የመለያ መስፈርቶች ተለይተው ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በቅንጅት የሚሰሩ የሶላር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች ጋር የአፈጻጸም ውይይት በተደረገበት ወቅት የሶላር አሰራጭ ድርጂቶች ቁጥር በየዙሩ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በዚህም ድርጅቶች ተለይተው ወደ ስራ መግባታው ተገልጿል።

እስካሁን ባለው ሂደት በድምሩ 62,635 የሶላር ቴክኖሎጂዎች የተሰራጩ ሲሆን በአጠቃላይ በአራተኛው ዙር የተለዩትን ድርጅቶች ጨምሮ፥ ወደ 205,637 የቤት ውስጥ ሶላር ቴክኖሎጂዎችን (Solar Home System) እና ምርታማነትን የሚያሳድጉ 2,544 የኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን (Productive Use of Energy) ለማሰራጨት የሚያስችል ውል ተፈርሟል።

የዘንድሮው አፈጻጸም ከባለፈው ዓመት የተሻሻለ ቢሆንም፥ ካለው እቅድ እና ድርጅቶቹ ራሳቸው ካቀዱት አንጻር ከዚህ በተሻለ መስራት እንደሚቻል በውይይቱ ላይ ተመላክቷል።

በአገሪቱ እየተከናወነ ባለው የሶላር ስርጭት ሂደት ላይ የግሉ ዘርፍ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስታውቆ፥ ድርጅቶቹ ያቀዱትን ስራ በአግባቡ እንዲተገብሩ ጥሪ በማቅረብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ለስራው መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር በሙሉ እንደሚያደርግ በድጋሚ አረጋግጧል።

የዕለቱ መድረክ ዋና ዓላማም በአፈጻጸም ላይ እያጋጠሙ ያሉ ዋና ዋና ተግዳሮቶችን በጋራ በመለየት፣ አፈጻጸሙን ከፍ የሚያደርጉ የጋራ መፍትሄዎችንና አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል፡፡

Share this Post