ኢትዮጵያና ጃፓን በኢነርጂ ልማትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ትብብራቸውን ለማጠናከር ተወያዩ
ኢትዮጵያና ጃፓን በኢነርጂ ልማትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ትብብራቸውን ለማጠናከር ተወያዩ
ህዳር 15/2019 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) – በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ኢር ድንቁ ስዩም ከጃፓን የንግድና ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ድርጅት (JETRO) ልዑካን ቡድን ጋር በኢነርጂ ልማት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በኢንቨስትመንት ዕድሎች ዙሪያ ተወያዩ።
በውይይቱ ወቅት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በዘላቂ ኢነርጂና በሌሎች ቁልፍ የልማት ዘርፎች ከፍተኛ እመርታ እያስመዘገበች መሆኗን ገልጸዋል። የልማት ውጤቶቹም ከዋና ከተማዋ ባሻገር በክልል ከተሞችና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተመዘገቡ መሆኑን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ 47 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ ፍርግርግ (Grid Electricity) ጋር በመገናኘት፣ 7 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከፍርግርግ ውጭ በሆኑ አማራጭ የኃይል ምንጮች (Off-grid Solutions) አማካኝነት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እያገኘ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም በገጠርና ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ ፍርግርግ ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ማስፋፋት ትልቅ የትብብር ዕድል እንዳለው አስረድተዋል። በጋራ ጥረት፣ በኢንቨስትመንትና ተገቢ የኃይል አማራጮችን በመጠቀም የገጠር ኤሌክትሪክ ሽፋንን ማሳደግና በርካታ ዜጎች አስተማማኝና ዘላቂ የኃይል አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል እንደሚቻልም ገልጸዋል።
የጃፓን ልዑካን ቡድን በበኩሉ የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመመልከትና የቅድመ-ኢንቨስትመንት ጉብኝት ለማድረግ ወደ ሀገሪቱ መጥተው መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም በአረንጓዴ ልማት፣ በታዳሽ ኃይል፣ በቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ፣ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋልና በሌሎች ተያያዥ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው አብራርተዋል።
በውይይቱ የኢትዮጵያን የኢነርጂ ሀብት በአግባቡ ለማልማት፣ የታዳሽ ኢነርጂ ምንጮችን ለማስፋፋት፣ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማሳደግና የዘርፉን የቴክኖሎጂ አቅም ለማጎልበት የሚያስችሉ የትብብር ዕድሎች ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጓል።
በተለይም የጂኦተርማል ኢነርጂ ልማት፣ የፀሐይና የንፋስ ኃይል አቅምን ማስፋፋት፣ የኃይል ማስተላለፊያና ስርጭት መሠረተ ልማቶችን ማዘመን እንዲሁም ዘመናዊ የኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅ የውይይቱ ዋና ትኩረቶች ነበሩ።
ጃፓን በኢትዮጵያ የጂኦተርማል ኢነርጂ ልማት ላይ ቀደም ሲልም የትብብር ልምድ ያላት ሲሆን፣ በጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ሥርዓት ግንባታ ላይ በጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ድርጅት (JICA) በኩል የፋይናንስ ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች።
በመሆኑም የሁለቱ ሀገራት ትብብር መጠናከር የኢትዮጵያን የኢነርጂ ሀብት ወደ ምርታማነት ለመቀየር፣ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማሳደግ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ለማስተዋወቅና ዘላቂ የኢነርጂ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል።