የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሴቶች የምግብ ዝግጅት ህብረት ሽርክና ማህበር አባላት አሰራራቸውን ይበልጥ ለማሻሻል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሴቶች የምግብ ዝግጅት ህብረት ሽርክና ማህበር አባላት አሰራራቸውን ይበልጥ ለማሻሻል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ
ህዳር፣ 15/2019 ዓ.ም(ው.ኢ.ሚ) -በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ስር የሚገኘው የሴቶች የምግብ ዝግጅት ህብረት ሽርክና ማህበር አባላት፣ የማህበሩን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴና የወደፊት አቅጣጫ አስመልክቶ ውይይት አካሂደዋል።
የውይይቱ ዋና ዓላማ የማህበሩን ዓላማና ግብ መሠረት በማድረግ እስካሁን የተመዘገቡ አበረታች ጥንካሬዎችን ይበልጥ ለማጠናከር፣ በአሰራር ሂደት የታዩ ክፍተቶችን በመለየት በፍጥነት እንዲስተካከሉ ለማድረግና ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ለማሻሻል ያለመ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የክቡር ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማሙሻ ኃይሉ የመመሥረቻ ሰነዱን በመገምገም ባቀረቡት ገለጻ፤ ማህበሩ በ2017 ዓ.ም የተቋቋመው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሴት ሰራተኞች ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ለማስቻል፣ ለሰራተኞች ጥራት ያለው የምግብ አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እንዲሁም የስራ ዕድል ለመፍጠር እንደሆነ አብራርተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽሕፈት ቤት «ገበያነሽ፣ ሸዋነሽና ጓደኞቻቸው ህብረት ሽርክና ማህበር» በሚል ስያሜ የንግድ ፈቃድ አግኝቶ የተቋቋመው ይህ ማህበር፣ በተሳካ ሁኔታ ወደ ስራ እንዲገባ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል የቁሳቁስ ግብዓት ግዢ፣ እንዲሁም ከውኃ፣ ከመብራትና ከቤት ኪራይ ክፍያ ነጻ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ልዩ ድጋፍ ተደርጎለታል። በአሁኑ ወቅት 124 አባላትና 7 የአመራር ኮሚቴ አባላት ያሉት ማህበሩ፤ ከአባላቱ በተሸጠ የአክሲዮን (ሼር) ድርሻ 835,000 (ስምንት መቶ ሰላሳ አምስት ሺህ) ብር ካፒታል ማሰባሰብ መቻሉ ተገልጿል።
በውይይቱ ወቅትም ማህበሩን ይበልጥ ዘመናዊ፣ አሳታፊና ውጤታማ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጓል። በዚህም መሠረት የማህበሩን ስያሜ ሁሉንም አባላት በሚወክል የጋራ መጠሪያ እንዲሆን ማስተካከልና የመመስረቻ ሰነዶቹን አሁን ካለው የአባላት ቁጥርና ከተሰበሰበው ካፒታል ጋር በሚመጣጠን መልኩ ማዘመን እንዲሁም የማህበሩን መተዳደሪያ ደንብ ተገቢውን ህጋዊ መሠረት እንዲይዝ በማድረግ ግልጽነት የሚፈልጉና ሠዋሰዋዊ እርምት የሚሹ ጉዳዮችን ማስተካከል እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በተጨማሪም በሚኒስቴሩ የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኦልቀባ ባሼ በማህበሩ ውስጥ የሚተላለፉ ቁልፍ ውሳኔዎች በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔና ይሁንታ ብቻ እንዲጸድቁ ማድረግ፣ መደበኛ የጠቅላላ ጉባኤ መድረኮችን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የማህበሩን ትርፍና ኪሳራ በግልጽ ለማወቅ መደበኛ የሂሳብ ኦዲት ማካሄድ፣ የአመራር ኮሚቴውን የሥልጣን ዘመንና የእያንዳንዱን የኮሚቴ አባል የስራ ድርሻ በግልጽ መወሰን፣ የአክሲዮን ሽያጭ ማስተዋወቂያ ቀነ ገደብን፣ የአክሲዮን ድርሻ አሰጣጥንና የሰው ኃይል ስምሪትን ይበልጥ ግልጽ ማድረግ እንዲሁም ያለ ዕቅድና በድንገት የሚካሄዱ የዕቃ ግዢዎችን በማስቀረት በታቀደ ስርዓት ብቻ መፈጸም እንደሚገባ አስገንዝበው ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በመጨረሻም በውይይቱ ወቅት የተነሱ የአሰራር ማሻሻያ ሀሳቦች ተቀባይነት አግኝተው ግልጽነት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ መሰጠቱ ለማህበሩ ቀጣይ ዕድገት ወሳኝ መሆኑ ተመላክቷል። የማህበሩ አመራር ኮሚቴም የታዩ ክፍተቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማረም የአባላቱን ተጠቃሚነትና የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጧል።