የውሃ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ኢ/ር አክሊሉ አዳኝ ከዘርፉ አመራሮች ጋር ተወያዩ

የውሃ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ኢ/ር አክሊሉ አዳኝ ከዘርፉ አመራሮች ጋር ተወያዩ

ጥቅምት 26/2019 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ.) የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአሰራር ቅልጥፍናን ለማምጣት እና ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር በሚል ቀደም ሲል በሁለት ሚኒስትር ዲኤታዎች ተከፍለው ሲከናወኑ የነበሩትን የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፎችን ወደ አንድ በማቀላቀል አዲስ መዋቅር ዘርግቷል።

ይህንኑ መዋቅራዊ ለውጥ ተከትሎ አዲሱ የዘርፉ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ኢ/ር አክሊሉ አዳኝ ከስራ መሪዎች እና ከፕሮጀክት አስተባባሪዎች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ትውውቅ በማድረግ የተግባር ውይይት አካሂደዋል።

በዚሁ የምክክር መድረክ ላይ በተቀናጀ ውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ በአቶ ላይነህ ይርዳው እና በሌሎች የስራ ኃላፊዎች አማካኝነት በዘርፉ ስር የሚገኙ ዋና ዋና ፕሮጀክቶችና የስራ ክፍሎች ገለጻ የቀረበ ሲሆን የጎርፍ መከላከል ስራዎች በየአካባቢው ሊከሰቱ የሚችሉ የጎርፍ አደጋዎችን ለመቀነስ እና የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት፤

የባዘርኔት ፕሮጀክት በተፋሰሶች ዙሪያ የውሃ ሀብት መረጃዎችን በቅርበት ለመከታተልና መሬት ለማውረድ የሚሰሩ ስራዎች፤

የተቀናጀ ውሃ ሀብት አስተዳደር (IWRM) የሀገሪቱን የውሃ ሀብት በዘላቂነት ከመጠቀምና ከመንከባከብ አንጻር የተከናወኑ ተግባራት እና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት ተደርጓል ።

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ክቡር ሚኒስትር ዲኤታ ኢ/ር አክሊሉ አዳኝ እንደተናገሩት፣ የተጀመሩ የልማትና የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በጋራ በመተባበር እና በመደጋገፍ እንደሚሰሩ ገልጸዋል ።

በመጨረሻም በዘርፉ ስር ያሉ ፕሮጀክቶችና የስራ ክፍሎች የተቀናጀ አሰራርን በመከተል የተጣለባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ሙሉ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

Share this Post