የዓለም ባንክ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ድጋፉን እንደሚያጠናክር ገለጸ
የዓለም ባንክ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ድጋፉን እንደሚያጠናክር ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25/2019 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የዓለም ባንክ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች እያደረገ ያለውን ድጋድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ክቡር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በጽህፈት ቤታቸው የዓለም ባንክ ተወካዮችን ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይቱ ላይ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒትር ዴኤታ አክሊሉ አዳኝ (ኢ/ር) እና የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒትር ዴኤታ ዶ/ር ኢንጅነር ድንቁ ስዩም ተገኝተዋል።
ለዓለም ባንክ ተወካዮች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ክቡር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)፤ ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር የምትሰራቸው ስራዎች ውጤታማ ናቸው ብለዋል።
በተለይ በዋን ዋሽ ፕሮግራም የሠራናቸው ስራዎች ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የሚሆን ውጤታማ ስራ ሰርተናል ሲሉ ገልጸዋል።
ውጤቱን ያመጣው በመንግሥት ጠንካራ ክትትል በመደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ በጀቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል መሰራቱ እና ተገቢው ክትትል መደረጉ ውጤታማ አድርጎናል ብለዋል።
የዓለም ባንክ ተወካዮች ቡድን መሪ ጁሊያን ቪክተር በበኩላቸው፤ ክቡር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በድጋሚ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሆነው በመሾማቸው የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ተቋማቸው ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በትብብር የሚሰራቸው የአንድ ቋት ብሔራዊ ዋሽ ፕሮግራም፣ ሁለተኛው የከተሞች የመጠጥ ውሃ ሳኒቴሽን ፕሮጀክት፣ የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት እና በሶስተኛው ምዕራፍ ዘላቂ የንጹህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ሀይጅን ተደራሽነት ፕሮጀክት ከአንዳንድ ተግዳሮቶች በስተቀር በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ መንግሥትና በልማት አጋሮች በጋራ የሚደገፈው የአንድ ቋት ብሔራዊ ዋሽ ፕሮግራም ከዓለም ባንክ ከተገኘው 300 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገንዘብ ለማንቀሳቀስ ማስቻሉን ጠቁመዋል።
በፕሮግራሙ በንጹህ የመጠጥ ውሃ እና በሳኒቴሽን ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል።
በፕሮግራሙ አንዳንድ ፕሮጀክቶች መዘግየት እንዳጋጠማቸው ገልጸው፤ ፕሮግራሙ ለተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መጠየቁን፣ የግዥ እና የካሳ ክፍያዎች እንዲከፈሉ እንዲሁም አካላዊ ስራዎችን ከፋይናንስ አፈጻጸም ጋር ማጣጣም እንደሚገባ አመልክተዋል።
በተመሳሳይ በከተሞች የሚገነቡ የፍሳሽ ዝቃጭ ማከሚያ ፕሮጀክት በተጠናከረ ክትትል እስከ ሰኔ ወር ድረስ 14 የማከሚያ ጣቢያዎች እንዲጠናቀቁ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።
በሌላ በኩል በግዥ ሂደትና በውል አስተዳደር በኩል መሻሻል መታየቱን ገልጸዋል።
የአካላዊ ስራዎች አፈፃፀምን ከፋይናንስ ወጪ ጋር ማጣጣም ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የፓምፕ ሙከራዎችን፣ የስራ ማረጋገጫና የክፍያ ሂደቶችን ማፋጠን፣ የቅድሚያ ክፍያዎችን ሂሳብ ማወራረድና ቀሪ የግዥ ሂደቶችን በወቅቱ ማጠናቀቅ ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ የገጠር የውሃ አቅርቦት ዲዛይን ማጠናቀቅ፣ የቀሩ የግንባታ ውሎችን መፈረም፣ የፋይናንስ ክፍያን ማፋጠንና በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየውን የነዳጅ አቅርቦት ችግር መፍታትም ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ሲሆኑ በቀጣይም የዓለም ባንክና የኢትዮጵያ መንግስት የጋራ የትግበራ ድጋፍና ግምገማ ተልዕኮዎችን ለማካሄድ ተስማምተዋል።
ውይይቱ የፕሮጀክቶቹን አፈፃፀምም በቅርበት ለመከታተል፣ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታትና የታቀዱ ውጤቶችን ለማሳካት የሚያግዝ ሲሆኑ የተጀመሩ የውሃና የንፅህና ስራዎችን በጥራትና በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ፣ የተመደበውን የፋይናንስ ሀብት በተገቢው ሁኔታ መጠቀምና የዜጎችን የንፁህ ውሃና የንፅህና አገልግሎት ተደራሽነት ማሻሻል ላይ ያተኮረ ነው።