የውሃ ሀብትን በዘላቂነት በማልማትና በመጠቀም የሀገር ውስጥ የውሃ ደህንነትን ከቀጠናዊ ትብብር ጋር በማጣመር ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለፀ
የውሃ ሀብትን በዘላቂነት በማልማትና በመጠቀም የሀገር ውስጥ የውሃ ደህንነትን ከቀጠናዊ ትብብር ጋር በማጣመር ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለፀ
ጥቅምት 20/2019 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ለአራት ቀናት ሲካሄድ በቆየው 3ኛው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት የማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ በዘርፉ ለተመዘገቡ ውጤቶችና ለተደረጉ የልማት ጥረቶች የነበራቸው አስተዋጽኦም ከፍተኛ እንደነበረ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የክቡር ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ሚካኤል መሀሪ ገለፁ።
እ.ኤ.አ በ2024 የተካሄደው የመጀመሪያው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት በታላቅ ትሩፋት ተነሳሽነት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በ2025 ደግሞ ለዘላቂ ልማት የውሃና የንፁህ ኢነርጂ አቅርቦትን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ውጤታማ ውይይቱ እንደነበረ ያስታወሱት ዶ/ር ሚካኤል 3ኛው የውሃና ኢነርጂ ሳምንትም ሳይንስን፣ ፈጠራንና ዲፕሎማሲን መሰረት ያደረጉ ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን፣ ወደ አረንጓዴ ኢነርጂ ሽግግር፣ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርና ዘላቂ ልማት ላይ ትኩረት ማድረጉንም ገልፀዋል።
በተለይም የውሃ፣ የኢነርጂ፣ የምግብና የስነ-ምህዳር ትስስርን ከፖሊሲ ወደ ተግባር በማሸጋገር የሀብት አጠቃቀምን ለማሻሻል በተቋሙ በኩል በርካታ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን በህዝብ ቁጥር መጨመርና በመሬት መራቆት ምክንያት የውሃ ደህንነት ተግዳሮቶች እየጨመሩ መምጣታቸውንም አክለዋል።
የውሃ ሀብትን በተቀናጀና በዘላቂነት ማልማት፣ የሀገር ውስጥ የውሃ ደህንነትን ማረጋገጥና በዓባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከል በፍትሀዊነትና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ የውሃ አጠቃቀምን ማጠናከር የሚጠይቅ መሆኑን አመልክተዋል።
የውሃ ሀብትን በዘላቂነት በማልማትና በመጠቀም የሀገር ውስጥ የውሃ ደህንነትን ከቀጠናዊ ትብብር ጋር በማጣመር ማረጋገጥ እንደሚገባ ያሳሰቡት ዶ/ር ሚካኤል የውሃ ሀብትን በሳይንሳዊ መረጃ፣ በተቀናጀ ፖሊሲና በቀጠናዊ ትብብር ማስተዳደር ለሀገራዊና ክልላዊ የውሃ ደህንነት መሠረታዊ መሆኑንም ጠቁመዋል።