ለውሃ እና ኢነርጂ አስተማማኝነት፤ በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ እና አጋርነት !
ለውሃ እና ኢነርጂ አስተማማኝነት፤ በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ እና አጋርነት !
አዲስ አበባ፣ጥቅምት 19/2019 ዓ.ም(ው.ኢ.ሚ)_የ3ኛው የኢትዮጵያ የውሃ እና ኢነርጂ ሳምንት አካል የሆነው 14ኛው የባለድርሻ አካላት መድረክ (Multi-Stakeholder Forum) መርሀ ግብር ተጀምሯል ።
በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚኒስቴሩ አማካሪ አቶ ደበበ ደፈርሶ ዕለቱ "ለወደፊት የውሃ እና ኢነርጂ አስተማማኝነት በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ እና አጋርነት ! "በሚል መሪ ሀሳብ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያግዙ ጠቃሚ ምክሮች እና ሀሳቦች የሚነሱበት መሆኑን ተናግረዋል።
የውሃ እና ኢነርጂ ጉዳዮች ለሰው ልጅ ስልጣኔ እድገት፣ ለዕለት ተዕለት ኑሮ፣ እንዲሁም ለወደፊት ህልውና ወሳኝ መሰረት ናቸው ያሉት አማካሪው በዚህ የውሃ እና ኢነርጂ ሳምንት የሚካሄደው የባለድርሻ አካላት መድረክ፣ በዘርፉ ላይ ለመወያየት እና ሀሳብ ለመለዋወጥ ትልቅ እድል ይፈጥራል ብለዋል።
መድረኩ ለሁሉም ዘርፎች አስተማማኝ የውሃ እና ኢነርጂ አቅርቦት ያለውን የወደፊት ሁኔታ ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት የሚካሄድበት ሲሆን ይህም ከዚህ ቀደም በተካሄዱ የጋራ ቴክኒካዊ ግምገማዎች እና ሌሎች ተከታታይ ጥረቶች ላይ የተገነባ መሆኑን አውስተዋል።
በመርሀ ግብሩ ተቋማትን፣ ባለሙያዎችን፣ የልማት አጋሮችን፣ ተመራማሪዎችን እና ሌሎች በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲን እና ጠንካራ አጋርነትን በማሳደግ ረገድ የጋራ ፍላጎት ያላቸውን ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ እናበረታታለንም ሲሉ አሳስበዋል ።
በመጨረሻም ለዚህ ዝግጅት መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥን ለማምጣት፣ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ በዕለቱ በመድረኩ በሚንሸራሸሩ ሀሳቦችና በሚቀርቡ ገለጻዎች ገንቢ ሀሳቦች እንደሚነሱ እና ጠቃሚ ግንዛቤዎች እንደሚገኙ አረጋግጠዋል ።