የካርቦን ፋይናንስ ለዘላቂ የውሃ አቅርቦት ልማት ተጨማሪ ዕድል ይፈጥራል።

የካርቦን ፋይናንስ ለዘላቂ የውሃ አቅርቦት ልማት ተጨማሪ ዕድል ይፈጥራል።

አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 18/2019ዓ.ም

የካርቦን ፋይናንስን በመጠቀም የፀሐይ ኃይል የውሃ አቅርቦት ሥርዓቶችን ማስፋፋትና ዘላቂነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚቻል በሦስተኛው የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሳምንት ሦስተኛ ቀን በቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ ተጠቆመ።

በ236 የፀሐይ ኃይል የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት ቦታዎች በዓመት 4.9 ሚሊዮን ሊትር የናፍጣ ነዳጅ መቆጠብ፣ 13,129 ቶን የካርቦን ዳይኦክሳይድ (CO₂) ልቀትን መቀነስና 633 ሚሊዮን ብር የነዳጅ ወጪ ማዳን እንደሚቻል በጥናቱ ተመላክቷል።

ከዚህም በተጨማሪ፣ የካርቦን ልቀት ቅነሳውን በታማኝነት በማረጋገጥና በካርቦን ገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት እንደሚቻል ተጠቁሟል።

ይሁንና፣ የካርቦን ገበያውን በተግባር ለማሳለጥ ዝርዝር ደንቦችን፣ የልቀት ቅነሳ መለኪያ ዘዴዎችን፣ የገቢ ክፍፍል ሥርዓቶችንና የገበያ ምዝገባ ሥርዓትን በተገቢው ሁኔታ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ጽሑፉ አመልክቷል።

ለዚህም የቀረቡት ምክረ ሐሳቦች የውሃ ፕሮጀክቶችን መረጃ በወጥነት መመዝገብ፣ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን በአንድ መርሐ ግብር ማቀናጀት፣ የካርቦን ቅነሳ ውጤቶችን በገለልተኛ አካል ማረጋገጥ፣ ተገቢ የካርቦን ገበያ ገዢዎችን ማፈላለግና ከሽያጩ የሚገኘውን ገቢ ለጥገና፣ ለመለዋወጫ ዕቃዎችና ለአዳዲስ የውሃ ሥርዓቶች ማዋልን ያካትታሉ።

በክልሎች ደረጃ ኦሮሚያና አማራ ከዓመታዊው የCO₂ ልቀት ቅነሳ ሦስት አራተኛውን ያህል ድርሻ እንደሚይዙ የቀረበው መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ የብሔራዊ ካርቦን ገበያ ስትራቴጂና በካርቦን ገበያ አዋጅ የተፈጠረውን ዕድል በመጠቀም፣ የፀሐይ ኃይል የውሃ ፓምፖችን ማስፋፋትና ታማኝ የካርቦን ገበያ አሠራርን ማጠናከር ለውሃና ኢነርጂ ዋስትና ወሳኝ መሆኑም ተገልጿል።

በአጠቃላይ፣ የካርቦን ፋይናንስን በተዓማኒ መረጃ፣ በግልጽ አሠራርና በተገቢው የቁጥጥር ሥርዓት መሠረት መጠቀም የፀሐይ ኃይል የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክቶችን ለማስፋፋት፣ የውሃና የኃይል ዋስትናን ለማጠናከርና ለአካባቢ ጥበቃ የሚኖረውን አስተዋፅኦ ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑ ተጠቁሟል።

Share this Post