ሶስተኛው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ሀገራችን ያላትን የውሃ ሀብት እንድናውቅ የሚደረገው ጥረት በትምህርት ሊደገፍ ይገባል ሲሉ ተማሪዎች ገለጹ፡፡
ጥቅምት16 /2019 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በሶስተኛው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት የተዘጋጀውን ኤግዚቢሽን በጎበኙበት ወቅት ያነጋገርነው የኢፉቦሩ ቡራዩ ልዩ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነው ተማሪ ሮብሰን ገዳ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ኤግዚብሽኑ ኢትዮጵያ በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የደረሠችበትን እና የወደፊት ራእዩዋን፣ ለቀጣዩ ትውልድ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ለመስጠት ምን ያህል እየተሰራ እንዳለ በመግለፅ ስንጠቀምበት በቀላሉ የሚገኝ የሚመስለን የውሃ ሀብት በምን አይነት መንገድ አልፎ ለተጠቃሚዎች እንደሚደርስ ያለው ጉዞ ስለውሃ የማውቀውን አመለካከት የቀየረ ነው ብሏል።
በማከልም ውድና አላቂ ሀብት የሆነን የውሃ ሀብትን በቁጠባና በንጽህና መጠቀም ከሁሉም ይጠበቃል ሲል መልእክቱን በማስተላለፍ ለቀጣይ ትውልድ ሀገራችን ያላትን የውሃ ሀብት እንድናውቅ የሚደረገው ጥረት በትምህርት ሊደገፍ ይገባል በማለት ሀሳቡን ገልጿል ፡፡
ተማሪ ሲፈን ተስፋየ በበኩሏ የውሃ ሀብታችን ማወቅ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ወሳኝ እንደሆነና ውሃ እንዴት ወደ ኤሌክትሪክ ሀይል እንደሚቀየር ማወቅ ትልቅ ነገር ነው ብላለች።
ቴክኖሎጂን በመጠቀም ውሃን ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ ያለው ስራም ጥሩ እንደሆነ ገልጻለች።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተማሪዎች በዚህ ልክ መጥተው ሀገራቸው ያላትን የውሃና ኢነርጂ ሀብት እንዲረዱ ማድረጉ ሊመሰገንና ሊበረታታ እንዲሁም ሌሎች ተቋማት ሊወስዱት የሚገባ ተሞክሮ ጭምር መሆኑንም አክለው ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ሁሉም ተማሪ ኤግዚቢሽኑን በመጎብኘት ሀገራችን በውሃና ኢነርጆ የደረሰችበትን ደረጃ ሊመለከቱ ይገባል በማለት መልእክቷን አስተላልፋለች።