ሳይንሳዊ ማስረጃንና ቅንጅታዊ አሰራርን መሠረት ያደረገ አሠራር ለውሃና ኢነርጂ ዋስትና ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።
አዲስ አበባ፦ ጥቅምት 16/02/2019 ዓ.ም ይህ የተገለጸው 3ኛው የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሳምንት በይፋ በተከፈተበት መድረክ ላይ ነው።
ለውሃና ኢነርጂ ዋስትና የተጠበቀለት የወደፊት ሁኔታ ለመፍጠር ሳይንሳዊ ማስረጃን መሠረት ያደረጉ ፖሊሲዎችን መከተል፣ በተቋማት መካከል ቅንጅትን ማጠናከርና ውጤታማ አጋርነቶችን መፍጠር ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።
የዘንድሮው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት «ለውሃና ኢነርጂ ዋስትና የተጠበቀለት የወደፊት ሁኔታ ሳይንሳዊ መሠረት ያላቸውን ፖሊሲዎችና አጋርነቶች ማሳደግ» በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ነው። በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች የሚገኙ የልማት አቅሞችን በተቀናጀ መልኩ ለመጠቀም፣ የዕውቀት ልውውጥን ለማጠናከርና ተግባራዊ መፍትሔዎችን ለማፍለቅ ያለመ ነው።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋበተወካያቸው በኩል በቀረበ የመክፈቻ ንግግር እንደተጠቀሰው ውሃና ኢነርጂ ለምግብ ዋስትና፣ ለሕዝብ ጤና፣ ለኢንዱስትሪ ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለአገራዊ እድገት መሠረታዊ ግብዓቶች ናቸው።
በመሆኑም የውሃና ኢነርጂ ልማትን በተናጠል ከማቀድ ይልቅ በተቀናጀ መልኩ መተግበር የልማት ጥቅሞችን ከፍ ለማድረግ፣ የሀብት ብክነትን ለመቀነስና የተፈጥሮ ሀብቶችን በዘላቂነት ለመጠቀም እንደሚያስችል ተመልክቷል።
ኢትዮጵያ ያላትን የውሃና የታዳሽ ኢነርጂ ሀብት ወደ ዘላቂ ልማትና ሁሉን አቀፍ ብልጽግና ለመቀየር ተገቢ የሀብት አስተዳደርን፣ ቆራጥ አፈጻጸምንና ውጤታማ የተቋማት ትብብርን ማጠናከር ያስፈልጋል።
በተለይም ተመጣጣኝ ዋጋ ያለውና አስተማማኝ የኢነርጂ አገልግሎትን ማስፋፋት፣ የውሃ አቅርቦትና የንጽህና አገልግሎቶችን ማሻሻል፣ የከርሰ ምድር ውሃንና የውሃ ምንጭ መገኛ ተፋሰሶችን መጠበቅ ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ቁልፍ ጉዳዮች መካከል መሆናቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም ሳይንሳዊ ምርምርን፣ ዲጂታል መረጃንና ዘመናዊ የመረጃ ትንተና ዘዴዎችን በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ በስፋት መጠቀም አስፈላጊ መሆኑም ተጠቁሟል።
የውሃ ፍሰትና የአየር ሁኔታ ክትትልን ማጠናከር፣ የተፋሰስ መረጃ ሥርዓቶችን ማሻሻል፣ የውሃ ጥራትን በተሻለ ሁኔታ መከታተልና አስተማማኝ የኢነርጂ መረጃዎችን መጠቀም አደጋዎችን ቀድሞ ለመለየት፣ የተሻሉ የልማት ኢንቨስትመንቶችን ለመምረጥና የልማት ውጤቶችን ለመገምገም ያግዛል።
የምርምር ውጤቶችና ሳይንሳዊ ዕውቀቶች በሰነዶችና በሪፖርቶች ላይ ብቻ እንዳይቀሩ፣ ወደ ፖሊሲ ውሳኔዎችና ተግባራዊ የልማት ሥራዎች እንዲቀየሩ በተመራማሪዎች፣ በፖሊሲ አውጪዎች፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ በባለሀብቶችና በማኅበረሰቡ መካከል ያለውን ትስስር ማጠናከር እንደሚገባም ተገልጿል።
የውሃና ኢነርጂ ዋስትናን ለማረጋገጥ የመንግሥት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት፣ የልማት አጋሮችና የማኅበረሰቡ የጋራ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑም ነው በአንክሮት የተገለጸው።
በዚህም መንግሥት ምቹ የልማት አካባቢን በመፍጠርና አመራር በመስጠት፣ የግሉ ዘርፍ ደግሞ ኢንቨስትመንትን፣ ቴክኖሎጂንና የሥራ ልምድን በማቅረብ ጉልህ ሚና ሊኖራቸው ይገባል።
በተለይም የውሃ፣ የኢነርጂ፣ የምግብና የሥነ-ምህዳር ትስስርን ያገናዘበ የተቀናጀ የልማት አቀራረብ መከተል ከእያንዳንዱ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ጥቅም ለማስገኘትና የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጪው ትውልድ ለማስጠበቅ ያስችላል።
ከዚህ በተጨማሪ፣ የጋራ ወንዞችን በተመለከተ በተገነባ ውይይት፣ በታማኝ መረጃና በትብብር ላይ የተመሠረተ አካሄድ መከተል ለቀጠናው ትስስር፣ ለጋራ ብልጽግናና ለሰላም አስፈላጊ መሆኑም ተመልክቷል።
በዚህ ረገድ የውሃ ዲፕሎማሲ የጋራ ተግዳሮቶችን ወደ የትብብርና የልማት ዕድሎች ለመቀየር ጠቃሚ ሚና አለው።
በመጨረሻም፣ ከ3ኛው የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሳምንት የሚጠበቀው ውጤት በውይይት ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ ወደ ተግባር የሚቀየሩ ምክረ ሐሳቦችን፣ የተጠናከሩ አጋርነቶችን፣ ለኢንቨስትመንት ዝግጁ የሆኑ ፕሮጀክቶችንና በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ ለማረጋገጥ የሚያግዙ ተግባራዊ ውሳኔዎችን ማስገኘት መሆኑንም ተገልጿል።
በመድረኩ የዴንማርክ አምባሳደር በኢትዮጵያ፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት፣ የፌዴራልና የክልል ተቋማት ተወካዮች፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍ ሀላፊዎች፤ ተመራማሪዎች፤ የአካዳሚክ ማኅበረሰብ አባላት፤ ተቋራጮችና አማካሪዎች፣ የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።