በውሃ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የቁጥጥር ምርመራ እና የውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን አስተዳደር የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተካሄደ ነው።
አዲስ አበባ — መስከረም 27 ቀን 2019 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ)
በምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን አገልግሎት ተደራሽነትን ለማፋጠን ያለመ የውሃ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የቁጥጥር ምርመራ እና የአስተዳደር የስልጠና መድረክ በአዲስ አበባ ጌትፋም ሆቴል እየተካሄደ ነው።
መድረኩን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአፍሪካ ህብረት ልማት ኤጀንሲ (AUDA-NEPAD) እና ከምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የውሃ እና ሳኒቴሽን ተቆጣጣሪዎች ማህበር (ESAWAS) ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን ዋና ዓላማውም እ.ኤ.አ. በ2030 ለሁሉም ዘላቂ የንጹህ ውሃ እና የሳኒቴሽን አቅርቦትን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረውን የተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግብ 6 (SDG 6) ለማሳካት የሚደረገውን እንቅስቃሴ መደገፍና ማፋጠን እንደሆነ ተገልጿል።
በመድረኩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ዶክተር ምትኩ በድሩ ፣ በኢትዮጵያ የውሃ አስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ ዋና ምሰሶ የሆነውን የውሃ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የቁጥጥር ጉዳይ ላይ ትኩረት በማድረግ በአንድነት ለመምከር መርሃ ግብሩ መዘጋጀቱን ገልጸው፣ ዘላቂ የውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎትን ለማረጋገጥ የአስተዳደር እና የቁጥጥር ስርዓትን ማጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።
በሚኒስቴሩ የከተማ መጠጥ ውሃ ጥናት፣ ዲዛይን፣ ግንባታና ክትትል ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ አዜብ ታደሰ በበኩላቸው፤ ራሱን የቻለ የዘርፉ አስተዳደር ስርዓት መመስረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ በከተማ የውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ተግዳሮቶችንም በዝርዝር ዳሰዋል። አያይዘውም ስራውን በህግ ለመደገፍ የሚያስችሉ ምቹ ህጋዊና ህገ-መንግስታዊ የስልጣን ውክልናዎችን፣ ለዘርፉ የሚሆኑ የተመረጡ የቁጥጥር ሞዴል አማራጮችን እንዲሁም ተቋማቱን በደረጃ ለማቋቋም የሚያስፈልገውን የምስረታ ሂደት ዑደት ለተሳታፊዎቹ አቅርበዋል።
በተጨማሪም የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የውሃ እና ሳኒቴሽን ተቆጣጣሪዎች ማህበር (ESAWAS) ዋና ዳይሬክተር ክብርት ይቮኔ ማጋዋ በመድረኩ ላይ የውሃ ሀብትን ፍትሃዊ አጠቃቀም፣ ጥራትን እና የአገልግሎት ሰጪዎችን ብቃት በህግ ለመቆጣጠርና ለመምራት የሚያስችለው የፈቃድ አሰጣጥ ስርዓት ላይ ያተኮረ ሰፊ ገለጻ ያቀረቡ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የውሃ ፈቃድ አሰጣጥ ስርዓት ልምዶችና ነባራዊ ሁኔታዎችና መፍትሄ የሚሹ ጉዳዮች ላይም ተሳታፊዎቹ በስፋት ተወያይተውበታል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ተቋማት ለህብረተሰቡ የሚያቀርቡት አገልግሎት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል የውሃ ጥራትና የጤና ደህንነትን መጠበቅ፣ የአገልግሎት ቀጣይነትና ሰዓትን ማረጋገጥ፣ የአገልግሎት ጥራት መመዘኛ መስፈርቶች እንደ ምሳሌ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
መድረኩ ላይ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተወከሉ የስራ ኃላፊዎች፣ የከተማ የውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ኢንተርፕራይዞች ዋና ስራ አስፈጻሚዎች፣ የክልል የውሃ ቢሮዎች አመራሮችና ተወካዮች፣ እንዲሁም የገጠር ባለብዙ-መንደር የውሃ አቅርቦት ኢንተርፕራይዞች ዋና ስራ ተሳታፊ ሆነዋል። በተጨማሪም የአዲስ አበባ፣ የድሬዳዋ እና የሐረር የውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ባለስልጣናት ዋና ስራ አስኪያጆች፣ የየዘርፉ የዴስክ ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ መርሃ ግብር በውይይቶቹ እና በሚሰጡት የስልጠና አጀንዳዎች አማካይነት የውሃ አገልግሎት ቁጥጥር ስርዓትን ለማጠናከር፣ በዘርፉ የሚታዩ የአስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ እና በባለድርሻ አካላት መካከል ጠንካራ የጋራ ስምምነት ለመፍጠር የሚያስችሉ ጉዳዮችና ሌሎች ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች እንደሚነሱ ይጠበቃል።
ስለተቋማችን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት
ፌስቡክ
https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p/
ቴሌግራም
http://t.me/mowieethiopia
ዌብሳይት
http://mowe.gov.et
X/ትዊተር
https://x.com/mowe_ethiopia
ዩቱዩብ
https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s
ቲክቶክ
tiktok.com/@mowetikto