የሕፃናት ማቆያ ማዕከሉ ለሴት ሠራተኞች የሥራ እፎይታ፣ ለሕፃናት የእድገት መሠረት መሆኑ ተገለጸ።

የሕፃናት ማቆያ ማዕከሉ ለሴት ሠራተኞች የሥራ እፎይታ፣ ለሕፃናት የእድገት መሠረት መሆኑ ተገለጸ። መስከረም 13/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሕፃናት ማቆያ ማዕከል ላለፉት አራት ዓመታት አገልግሎት ሲያገኙ ለቆዩ 14 ሕፃናት የሽኝት መርሃ ግብር ተካሄደ። የሕፃናቱ የሽኝት መርሃ ግብር የተካሄደው ዕድሜያቸው ለቅድመ መደበኛ ትምህርት በመድረሱ ሲሆን፣ ለቀጣዩ የትምህርትና የእድገት ምዕራፍ እንዲሸጋገሩ መልካም ምኞት ለመግለጽ መሆኑ ታውቋል። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የውብዳር አሚኖ እንደገለጹት፣ የሕፃናት ማቆያ ማዕከሉ የተቋሙ ሴት ሠራተኞች ስለልጆቻቸው ሳይጨነቁ ሥራቸውን በእርጋታ እንዲያከናውኑ በማስቻል የሴት ሠራተኞችን የሥራ ተሳትፎና የሙያ አቅም ለማጎልበት ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ብለዋል። በማዕከሉ ሕፃናት በሰለጠኑ የሕፃናት እንክብካቤ ባለሙያዎች አገልግሎቱን እያገኙ ጤናማ በሆነ ፣ ምቹና አስተማማኝ ሁኔታ እንዲያድጉ እየተደረገ መሆኑንም ወ/ሮ የውብዳር ገልጸዋል። በማዕከሉ የሚሰጠው የሕፃናት እንክብካቤ ለሴት ሠራተኞች እፎይታ ከመፍጠር ባሻገር ሕፃናት ጤናቸው ተጠብቆ በእውቀትና በክህሎት እንዲያድጉ መሠረት የሚጥል አገልግሎት መሆኑን ወ/ሮ የውብዳር ጠቁመዋል። በኮሪደር ግንባታ ምክንያት የቀድሞው የሕፃናት ማቆያ ቢነሳም፣ ከበፊቱ በተሻለ ምቹ፣ ዘመናዊና ለሕፃናት ተስማሚ በሆነ መልኩ አዲስ ማዕከል እየተገነባ መሆኑን አክለው ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት አዲስ ገቢ ሕፃናትን ጨምሮ 16 ሕፃናት በማዕከሉ አገልግሎት እያገኙ መሆኑንም ወ/ሮ የውብዳር ገልጸዋል። የሕፃን ሚናስ እንግዱ እናትና በውሃ ብክለት ክትትልና ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያነት እያገለገሉ ያሉት ወ/ሮ ቆንጂት መርሻ፣ ልጃቸው የ6 ወር ሕፃን እያለ ወደ ማዕከሉ በማምጣት ሥራቸውን በእርጋታ ማከናወን እንደቻሉ እና ለአራት ዓመታት በማዕከሉ የተሟላ እንክብካቤ አግኝቶ አሁን ለቅድመ መደበኛ ትምህርት በመድረሱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል። “ልጄ ከዚህ ማዕከል በእንክብካቤ አድጎ ለትምህርት የደረሰ መሆኑ እንደ እናት ትልቅ ኩራትና ደስታ ፈጥሮልኛል ያሉት ወ/ሮ ቆንጂት ነገ ልጄ በውሃ ዘርፍ ቢሰማራ፣ ያደገበትንና የተንከባከበውን ተቋም እንደማይረሳ እምነቴ ነው። ይህ ማዕከል ለልጄ እንክብካቤ ብቻ ሳይሆን ለወደፊት ሕይወቱም መሠረት ጥሏል” ብለዋል። ወ/ሮ ቆንጅት በተለይም በመስክ ሥራ ላይ በሚሆኑበት ወቅት ባለቤታቸውም የተቋሙ ሠራተኛ በመሆናቸው ልጃቸውን ወደ ማዕከሉ በማምጣት አገልግሎቱን በማግኘታቸው ትልቅ እፎይታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል። በተለይ የመስክ ሥራ ሲኖረኝ በልጄ ላይ የሚኖረኝን ጭንቀት ቀንሶልኛል፤ ሥራዬንም በእርጋታ እንድሠራ አስችሎኛል” ብለዋል። በማዕከሉ ልጃቸውን በእናትነት በመንከባከብ፣ በፍቅርና በትዕግሥት ላሳደጉት የሕፃናት እንክብካቤ ባለሙያዎች እንዲሁም ለስራ አስፈጻሚዋ ለወ/ሮ የውብዳር አሚኖ ወ/ሮ ቆንጅት ልዩ ምስጋና አቅርበዋል። “ለልጄ የሰጣችሁት እንክብካቤ ከሙያዊ አገልግሎት በላይ የእናትነት ፍቅር የተሞላበት ነበር። ዛሬ ልጄን ለትምህርት ስሸኘው የማዕከሉን ባለሙያዎች ያለምንም ማጋነን እንደ ልጄ ሁለተኛ እናቶች ነው የማያቸው” ሲሉም ምስጋናቸውን ገልጸዋል። የሁለት መንትዮች እናትና የንብረት አስተዳደር ባለሙያ ወ/ሮ ሜሮን ጎንፋ በበኩላቸው፣ በማዕከሉ ባሳለፉት አራት ዓመታት ከአመራሩ ጀምሮ እስከ ተንከባካቢዎቹ ድረስ በነበረው አቀባበልና አገልግሎት አሰጣጥ መደሰታቸውን ገልጸዋል። የመልእክት ሠራተኛና የሕፃን ናርዶስ ኦላና እናት ወ/ሮ ሌሊሴ ዋቅጋሪ በበኩላቸው፣ ልጃቸውን የሚይዝላቸው አማራጭ በማጣታቸው ወደ ማዕከሉ በማምጣት ሥራቸውን በእርጋታ ለመሥራት ያገኙት እፎይታ በቃላት ሊገለጽ እንደማይችል ገልጸዋል። በአዲስ መልክ ምቹና ማራኪ ሆኖ እየተገነባና እየተደራጀ የሚገኘው የሕፃናት ማቆያ ማዕከል፣ በቀጣይ ለተቋሙ ሴት ሠራተኞች የተሻለ የሥራ እፎይታ በመፍጠር እንዲሁም ለሕፃናት ጥራት ያለውና የተሻለ እንክብካቤ ለመስጠት የሚያስችል ሁኔታን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። ስለተቋማችን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ፌስቡክ https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p/ ቴሌግራም http://t.me/mowieethiopia ዌብሳይት http://mowe.gov.et X/ትዊተር https://x.com/mowe_ethiopia ዩቱዩብ https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s ቲክቶክ tiktok.com/@mowetikto

Share this Post