የተቋማዊ እሴቶችን ከውጤታማ አፈጻጸም ጋር ማስተሳሰር ለአዎንታዊ የሥራ ባህል ግንባታ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።

የተቋማዊ እሴቶችን ከውጤታማ አፈጻጸም ጋር ማስተሳሰር ለአዎንታዊ የሥራ ባህል ግንባታ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ። መስከረም 13 ቀን 2019 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) የተቋማዊ እሴቶችን ከዕለታዊ የሥራ አፈጻጸም ጋር በማስተሳሰር አዎንታዊ፣ ተጠያቂነትን የሚያጎለብትና ውጤታማ የሥራ ባህል መገንባት እንደሚገባ ተገለጸ። ይህ የተገለጸው “የተቋማዊ እሴቶችና የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ውህደት ለአዎንታዊ የሥራ ባህል” በሚል ርዕስ ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮችና ሠራተኞች በተሰጠ ስልጠና ላይ ነው። በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክቡር ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ማሙሻ ሀይሉ የአንድ ተቋም ስኬት በአደረጃጀትና በሥርዓት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ በሠራተኞች እሴት፣ ባህሪ፣ ተጠያቂነትና ለሕዝብ በሚሰጡት የአገልግሎት ጥራት እንደሚወሰን ገልጸዋል። በመሆኑም በሥራ ቦታ ታማኝነትን፣ ፍትሐዊነትን፣ ትብብርን፣ ተጠያቂነትንና ለውጤት ያለውን ቁርጠኝነት ማሳደግ የሁሉም የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አቶ ማሙሻ አስገንዝበዋል። ሠራተኞች በስልጠናው የሚያገኙት እውቀት በተግባር በመተርጎም የተሻለ የሥራ ባህል በመገንባት ለተቋሙና ለሕዝብ የተሻለ አገልግሎት እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪም በስልጠናው በንቃት እንዲሳተፉና ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ አሳስበዋል። ስልጠናውን የሰጡት የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኦልቀባ ባሼ በበኩላቸው፣ የተቋም እሴቶች በሰነድ ወይም በመመሪያ ብቻ የሚወሰኑ ሳይሆን፣ በየዕለቱ በሚፈጸሙ የሥራ ተግባራት ሊገለጹና ከተቋማዊ ውጤት ጋር ሊተሳሰሩ እንደሚገባ አብራርተዋል። በስልጠናው የተቋሙ እሴቶች የሆኑት ጥራት ያለው አገልግሎት፣ አዲስ ሀሳብና ፈጠራ፣ ብቃትና መፍትሄ አፍላቂነት፣ እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት፣ ጽናትና ቁርጠኝነት፣ አካባቢ ጥበቃና ዘላቂ ልማት በዝርዝር ተብራርተዋል። በተጨማሪም ሁልጊዜ መማርና እውቀትን ማሳደግ፣ የሥራ ሥነ-ምግባርን መጠበቅ፣ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን መጸየፍ የተቋማዊ እሴቶች አካል መሆናቸውንም አክለው ገልጸዋል። አቶ ኦልቀባ እሴቶች ውጤት የሚያመጡት በዕለት ተዕለት የሥራ አፈጻጸም ውስጥ ሲተገበሩ መሆኑን ገልጸው፣ የእያንዳንዱ ሠራተኛ የግል ሥነ-ምግባር ከተቋሙ እሴቶች ጋር ሲጣመር የተሻለ ተቋማዊ ውጤት እንደሚመጣ አብራርተዋል። “የግል ሥነ-ምግባር + የተቋም እሴት = የላቀ ተቋማዊ ውጤት” የሚለውን መርህ በማንሳት፣ እሴቶችን በተግባር ማዋሃድ የሥራ ባህልን ከማሻሻል ባሻገር የተቋሙን የአገልግሎት ጥራትና ውጤታማነት እንደሚያሳድግም ገልጸዋል። በስልጠናው የተቋሙ እሴቶች ከፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ሕጋዊ ግዴታዎችና የሥራ ሥነ-ምግባር መርሆች ጋር በማስተሳሰር ተብራርተዋል። ይህም ሠራተኞች ሕግን በማክበር፣ ሙያዊ ሥነ-ምግባርን በመጠበቅና ተጠያቂነትን በማስፈን የተቋሙን ተልዕኮ በተሻለ ሁኔታ እንዲያሳኩ የሚያግዝ መሆኑን ነው አቶ ኦልቀባ የጠቆሙት። ተቋማዊ እሴቶች በዕለት ተዕለት የሥራ አፈጻጸም ውስጥ በተግባር ሲዋሃዱ ተጠያቂነትን፣ ትብብርን፣ ፈጠራንና ውጤታማነትን በማጎልበት የተሻለ የሥራ ባህልና የላቀ ተቋማዊ ውጤት ለማምጣት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው በስልጠናው ተገልጿል። በስልጠናው በርካታ ሀሳብ አስተያየቶች ተነስተው ሰፊ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን "እሴቶቻችንን በመተግበር ተቋማችንን እናሳድግ"! "ጥራት ያለው አገልግሎት ፣ ታማኝነትና ፈጠራ የእለት ተእለት ባህላችን ይሁን!" የሚሉት ሞቶዎች ደግሞ የእለቱ የቃል ኪዳን ጥሪ ናቸው። ስለተቋማችን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ፌስቡክ https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p/ ቴሌግራም http://t.me/mowieethiopia ዌብሳይት http://mowe.gov.et X/ትዊተር https://x.com/mowe_ethiopia ዩቱዩብ https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s ቲክቶክ tiktok.com/@mowetikt

Share this Post