የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት የመካከለኛ ጊዜ ግምገማ ተካሄደ

የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት የመካከለኛ ጊዜ ግምገማ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣መስከረም 4/2019 ዓ.ም(ው.ኢ.ሚ). — በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚመራው የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት የመካከለኛ ጊዜ ግምገማ (Mid-Term Review Mission) ከመስከረም 4 እስከ 15 ቀን 2019 ዓ.ም. በተለያዩ መርሀ ግብሮች እየተካሄደ የሚቆይ ይሆናል።

ግምገማው ፕሮጀክቱ እስካሁን ያስመዘገበውን አፈጻጸም፣ የተከናወኑ ሥራዎችን፣ የተገኙ ውጤቶችን፣ ተግዳሮቶችንና ክፍተቶችን በመገምገም፣ በቀሪው የፕሮጀክቱ ዘመን ሊከናወኑ የሚገቡ ሥራዎችንና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለመለየት ያለመ ነው።

የፕሮጀክቱ አፈጻጸም በሰነድና በውይይት ብቻ ሳይሆን፣ በመስክ ደረጃም እየተገመገመ የሚካሄድ ሲሆን፣ የመካከለኛው አዋሽ አሚባራ ኢምባንክመንት ጉብኝት እና የአርባምንጭ ኩልፎ ጉብኝት የመስክ ምልከታ እንደሚካሄድባቸው ታውቋል።

እነዚህ የመስክ ጉብኝቶች በፕሮጀክቱ ስር የተከናወኑ የጎርፍ መከላከያ ሥራዎችን በተግባር ለመመልከት፣ የሥራዎቹን አፈጻጸምና ጥራት ለመገምገም እንዲሁም ከመስክ የሚነሱ ተግዳሮቶችንና ተጨማሪ ፍላጎቶችን ለመለየት ጠቃሚ ይሆናሉ።

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ተመስገን ከተማ ፕሮጀክቱ እስካሁን ያስመዘገበውን አፈጻጸም፣ የተከናወኑ ሥራዎችን፣ ቁልፍ ስኬቶችንና በቀጣይ የሚከናወኑ ሥራዎችን የያዘ ሪፖርት ለመድረኩ አቅርበዋል።

በግምገማው የሃይድሮሎጂና ሜትሮሎጂ መረጃ አሰባሰብና አጠቃቀም፣ የጎርፍ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ እንዲሁም የአካባቢና ማህበራዊ ስጋት አስተዳደር ሥራዎች በትኩረት እየተመረመሩ ነው።

የዓለም ባንክ የቴክኒካል ቡድን መሪ ሚስተር ሱራብ በቀረበው ሪፖርት ላይ አስተያየት በመስጠት፣ ተጨማሪ መረጃና ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የተጠናቀቁ ሥራዎችና የተገኙ ስኬቶች ከታቀዱ ዓላማዎች አንጻር እየተመዘኑ፣ ያሉ ክፍተቶችና ተግዳሮቶች እየተለዩ ነው። የቀሩ ሥራዎችም በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቁ በሚያስፈልጉ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው።

የግምገማው ሂደት ሲጠናቀቅ የመጨረሻ ግኝቶች፣ ምክረ ሀሳቦችና ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀርቡ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱም የጎርፍ አደጋን የመከላከልና የመቆጣጠር አቅምን ለማጠናከር በተለያዩ መርሐ ግብሮች ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ፌስቡክ

https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p/

ቴሌግራም

http://t.me/mowieethiopia

ዌብሳይት

http://mowe.gov.et

X/ትዊተር

https://x.com/mowe_ethiopia

ዩቱዩብ

https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s

ቲክቶክ

tiktok.com/@mowetikto

Share this Post