በአዋሽ ተፋሰስ ዘላቂና ፍትሃዊ የውሃ ምደባ ሥርዓት ላይ ውይይት ተደረገ።
አዳማ፣ ጳጉሜን 2/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ.) የአዋሽ ተፋሰስ የውሃ ሀብትን በፍትሃዊነት ፣ ቀልጣፋና ዘላቂ መንገድ በመመደብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል የውሃ ምደባ ሥርዓት ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረግ ውይይት ተደረገ።
የውይይቱ ዓላማ በአዋሽ ተፋሰስ ያለውን የውሃ ሀብት ለተለያዩ የውሃ ተጠቃሚ ዘርፎች በተቀናጀ መልኩ ለመመደብ እየተደረገ ያለውን ጥረት የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የባለድርሻዎችን ግብዓት ማሰባሰብና የጋራ መግባባት መፍጠር ነው።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አጠቃቀምና ፍቃድ ዴስክ ኃላፊ አቶ ጨመዳ ቶሊ፣ ውሃ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ልማት መሠረታዊ ሀብት መሆኑን ጠቁመው፣ የውሃ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ የውሃ ሀብትን በዕቅድ፣ በሳይንሳዊ መረጃና በተቀናጀ አስተዳደር መምራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
አዋሽ ተፋሰስ የውሃ ሀብት ለመጠጥ ውሃ፣ ለመስኖ ልማት፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለኢነርጂ ልማትና ለሌሎች የልማት አገልግሎቶች የሚውል በመሆኑ፣ እየጨመረ የመጣውን የውሃ ፍላጎት ከሚገኘው የውሃ አቅርቦት ጋር ማመጣጠን የምደባ ሥርዓቱ ቁልፍ ተግባር እንደሆነም ተጠቁሟል።
በዚህም የውሃ ምደባ ሥርዓቱ የተፋሰሱን የውሃ መጠንና ፍላጎት፣ የተለያዩ የውሃ አጠቃቀሞች፣ የአካባቢ ፍሰት ፍላጎት፣ የድርቅና የጎርፍ ስጋት እንዲሁም የወደፊት የውሃ ፍላጎትን በማገናዘብ ሊተገበር እንደሚገባ ተገልጿል።
በተለይም ውሃን የሚጠቀሙ ተቋማት፣ ክልሎች፣ የተፋሰስ ተቋማት፣ የግል ዘርፍ፣ የአርሶ አደርና አርብቶ አደር ማህበረሰቦች እና ሌሎች ባለድርሻዎች በሂደቱ የሚኖራቸው ተሳትፎ የምደባ ሥርዓቱን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ቁልፍ መሆኑም ተገልጿል።
በሁለቱ ቀናት ውይይት የአዋሽ ተፋሰስ የውሃ አቅርቦትና ፍላጎት፣ የውሃ ምደባ መርሆዎችና የሕግ ማዕቀፍ፣ የውሃ አጠቃቀም ፈቃድ፣ የውሃ ክፍፍል ቅድሚያና አስተዳደር፣ የተፋሰስ ደረጃ የውሃ ምደባ፣ የአዋሽ ተፋሰስ የደረቅ ወቅት የውሃ ምደባ ዕቅድ ይዘትና አተገባበር፣ እንዲሁም የውሃ ምደባ ትግበራ ክትትልና ግምገማን በሚመለከት በቀረቡ ሪፖርቶች ላይ ሰፊ ውይይት ይደረጋል።
በመድረኩ የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ የአፋር ክልል ውሃና ኢነርጂ፣ መስኖና ቆላማ እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮዎች፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤት እንዲሁም የተለያዩ የውሃ ተጠቃሚዎች እየተሳተፉ ነው።
የሁለቱ ቀናት ውይይት ውጤት በአዋሽ ተፋሰስ የውሃ ሀብትን በተቀናጀ፣ ፍትሃዊ፣ ግልጽና ዘላቂ መንገድ ለመመደብና ለመጠቀም ጠንካራ መሠረት እንደሚፈጥርም ተጠቁሟል።
ስለተቋማችን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት
ፌስቡክ
https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p/
ቴሌግራም
http://t.me/mowieethiopia
ዌብሳይት
http://mowe.gov.et
X/ትዊተር
https://x.com/mowe_ethiopia
ዩቱዩብ
https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s
ቲክቶክ
tiktok.com/@mowetikto