የበሻሻ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የጋራ የመስክ ምልከታ ተካሄደ
በሻሻ:-ጳጉሜ 02/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ የተመራ ቡድን፣ የበሻሻ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የግንባታ ሂደት ያለበትን ደረጃ ለመገምገም የመስክ ምልከታ እና ውይይት አካሂዷል።
በምልከታው ወቅትም የፕሮጀክቱን ቁጥጥር የሚያካሂዱት የባለሙያዎችና ቡድን እዲሁም የፕሮጀክት አስተባባሪዋ ወ/ሮ አዜብ ታደሰ ስለፕሮጀክቱ ለእንግዶቹ ጠቅለል ያለ ገለፃ አድርገዋል፡፡
ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ የግንባታ ውል ከተፈጸመበት ጊዜ አንጻር አሁን ላይ የደረሰበት ደረጃ በጣም የሚያበረታታ እና በፕሮጀክት አፈጻጸም ረገድ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው።
ክቡር አምባሳደር አክለውም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ያሉ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የቴክኒክ ባለሙያዎች ከተቋራጩ ጋር በቅንጅት፣ በከፍተኛ አመራር እና ቁርጠኝነት ፕሮጀክቱን ለዚህ ደረጃ ማብቃታቸውን በመጥቀስ ምስጋናና አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ በታቀደው አጭር ጊዜ እንዲያልቅ ተቋራጩ የስራ መርሃ ግብር እንዲያቀርብ፤ እንዲሁም ሱፐርቪዥን ቡድኑ በቀረበው መሰረት ክትትል እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡
የጎማ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ፉአድ በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለፕሮጀክቱ መሳካት ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ የስራውን ፈጣን ሂደት አድናቀዋል።
በተጨማሪም ተቋራጩ ባሳየው ጠንካራ አፈጻጸም በበሻሻ አካባቢ "በክረምት ወቅት ስራ መስራት አይቻልም" የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት የቀየረና በማይመቹ ሁኔታዎች ውስጥም ውጤታማ ስራ ማከናወን እንደሚቻል አቶ ፉአድ ገልጸዋል።
አቶ ፉአድ አክለውም ለፕሮጀክቱ ስኬት እንቅፋት የሚሆኑ ማናቸውንም ችግሮች ለመፍታት አስተዳደሩ ሁልጊዜም ከጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል።
ከገንዘብ ሚኒስቴር ክቡር አቶ ብርሃኑ አንበስ በበኩላቸው የፕሮጀክቱን ጥሩ አፈጻጸም በመጥቀስ ስራው ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶት ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።
አፈጻጸሙ የተገኘውን የበጀት ድጋፍ በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ወደፊት ለሚሰሩ ሌሎች ፕሮጀክቶችም ትልቅ ማሳያ እንደሚሆን የገለፁት አቶ ብርሃኑ ስራው ቃል በተገባው መሰረት እንዲጠናቀቅም መልካም አሳስበዋል፡፡
ከክልል ውሃ ቢሮ አቶ ዲሳሳ ጉደታ ፕሮጀክቱ እያሳየ ያለው የግንባታ ፍጥነትና በታቀደለት ጊዜ መጠናቀቁ ለሌሎች ተመሳሳይ ስራዎች መልካም እድል የሚፈጥር እና ተጨማሪ የግራንት ድጋፎችን ለማግኘት መንገድ የሚያመቻች መሆኑን ገልጸዋል።
በመጨረሻም ተቋራጩ ስራውን ከዚህ በበለጠ አጠናክሮ በመቀጠል ፕሮጀክቱን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲያጠናቅቅ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።