ዘላቂ ልማት ለሀገራዊ ማሠራራት

ዘላቂ ልማት ለሀገራዊ ማሠራራት

ነሐሴ/29/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ኢትዮጵያ በልማት ጉዞዋ እያስመዘገበች ያለውን ውጤት የሚያሳይ የፎቶ አውደ ርዕይ ተከፈተ

ኢትዮጵያ በውሃና ኢነርጂ፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በከተማና መሠረተ ልማት፣ በግብርና እና በሌሎች የልማት ዘርፎች እያስመዘገበች ያለውን ውጤትና የለውጥ ጉዞ የሚያሳይ የፎቶ አውደ ርዕይ ዛሬ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን አካዳሚ በይፋ ተከፍቷል።

የፎቶ አውደ ርዕዩ በሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን፣ የተገኙ ውጤቶችንና የተፈጠሩ አዳዲስ ዕድሎችን በምስል በማቅረብ የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ ለማሳየት ያለመ ነው።

በመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች፣ የተለያዩ ዘርፎች ተወካዮችና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ተገኝተዋል። ተሳታፊዎቹም አውደ ርዕዩ የሀገሪቱን የልማት ለውጥ በተጨባጭ ለማየት የሚያስችልና ቀልብ የሚስብ መሆኑን ገልጸዋል።

በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ የምርት ውጤቶች፣ በኢነርጂው ዘርፍ የተገነቡ የኃይል መሠረተ ልማቶች፣ እንዲሁም ከሀገር አልፈው ለጎረቤት ሀገራት የሚደርሱ የኢነርጂ አቅርቦቶች የኢትዮጵያን አዲስ የልማት አቅጣጫ የሚያመላክቱ እንደሆኑ ተጠቁሟል።

በተመሳሳይ፣ ከተሞች የዘመኑን የከተማ ልማት ስታንዳርድ በመጠበቅ እየተስፋፉ መምጣታቸው፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ እያሳየ ያለው እመርታ እንዲሁም በመሠረተ ልማት የሚታዩ ለውጦች የሀገሪቱን የልማት አቅም እያሳደጉ ያሉ ውጤቶች መሆናቸው በአውደ ርዕዩ ተስተውሏል።

እነዚህ ውጤቶች ኢትዮጵያ ከተለመዱት የችግርና የእርዳታ ትርክቶች በመሻገር፣ በራሷ አቅም ልማትን የማስፋትና ዘላቂ ዕድገትን የማረጋገጥ ጉዞ ላይ መሆኗን የሚያሳዩ ናቸው።

ኢትዮጵያ አዲሲቷ የተስፋ አድማስ ናት፤ ዛሬ የምታሳየው ውጤት የነገ ብልፅግና መሠረት ነው።

ዘላቂ ልማት ማለት የአንድ ዘርፍ ስኬት ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ ዘርፎች በተቀናጀ መልኩ የሚፈጥሩት ሀገራዊ ለውጥ ነው። የፎቶ አውደ ርዕዩም ይህንኑ እውነታ በምስል በማስመስከር “ኢትዮጵያ በእውነት እያሠራራች ነው” የሚል መልዕክት አስተላልፏል።

የዛሬው ሥራ የዘላቂ ልማት መንገድን ለማጠናከር፣ የተገኙ ውጤቶችን ለማስተዋወቅና የሀገራዊ ማሠራራት ሂደቱን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማሸጋገር የሚያበረታታ መሆኑ ተገልጿል።

Share this Post