የጎርፍ አደጋ ቅነሳ ሥራዎችን በጥናት ለመምራት ትኩረት ተሰጥቷል
የጎርፍ አደጋ ቅነሳ ሥራዎችን በጥናት ለመምራት ትኩረት ተሰጥቷል
አርባምንጭ፦ ነሐሴ 16/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) በስምጥ ሸለቆ ሐይቆችና በኦሞ–ጊቤ ወንዝ ተፋሰሶች የሚከሰቱ የጎርፍ አደጋዎችን በዘላቂነት ለመቀነስ በጥናት የተለዩ ተጋላጭና የቅድሚያ ቅድሚያ ቦታዎችን በመለየት ለመተግበር ትኩረት ተሰጥቷል። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎችን በጥናት በመለየት የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችሉ የተቀናጁ የጎርፍ መከላከል ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በአርባምንጭ ሀይሌ ሪዞርት እየተካሄደ ባለው የግምገማ ወርክሾፕ በሁለቱ ተፋሰሶች የጎርፍ አደጋ ቅነሳ ለማድረግ የተዘጋጁ ጥናቶች በባለሙያዎችና በባለድርሻ አካላት እየተገመገሙ ሲሆን፣ የተገኙ ምክረ ሀሳቦችም ለቀጣይ ሥራዎች እንደ ግብዓት እየተወሰዱ ነው።
የጎርፍ አደጋ ቅነሳ ሥራው ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ ቢሮ፣ ከአደጋ ስጋት ኮሚሽን፣ ከአማካሪዎችና ከሌሎች ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተተገበረ ይገኛል። ይህም ሥራዎቹ በሳይንሳዊ ጥናት፣ በአካባቢያዊ ተሞክሮና በአደጋ ስጋት መረጃ ላይ እንዲመሠረቱ የሚያግዝ መሆኑ ተመልክቷል። በዚህ ትብብር ዩኒቨርሲቲዎች በጥናትና በሳይንሳዊ ትንተና፣ የክልሉ ውሃ ቢሮ በአካባቢው የውሃ ሀብትና የተፋሰስ አስተዳደር እውቀት፣ አደጋ ስጋት ኮሚሽኑ ደግሞ በአደጋ ስጋት መረጃና ምላሽ ላይ ያለውን ሙያዊ ግብዓት እያበረከቱ ነው።
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ተመስገን ከተማ እንደገለጹት፣ የጎርፍ አደጋ ቅነሳ ከአጭር ጊዜ የአደጋ ምላሽ በተጨማሪ ዘላቂ የሆነ የተቀናጀ ዕቅድና በጥናት የተደገፈ መፍትሔ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ተጋላጭ አካባቢዎችን በመለየት ተገቢ ሥራዎችን በቅድሚያ ለመተግበር ትኩረት ተሰጥቷል።
እስካሁን በርካታ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ሥራ በመከናወኑ፣ የሰዉ ህይወት ማዳን የሥራ ዕድሎች መፈጠራቸውና የእርሻ መሬትን ከጎርፍ አደጋ ለመጠበቅ መቻሉንና ሌሎች በርካታ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አብራርተዋል። በቀጣይም በጥናት የተለዩ የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የጎርፍ አደጋ ቅነሳ ሥራዎችን በማጠናከር ማህበረሰቡን፣ የእርሻ መሬቶችንና የአካባቢውን ልማት ከጎርፍ አደጋ የመጠበቅ ሥራው እንደሚቀጥል አጽንኦት ተሰጥቶበታል።
ፌስቡክ https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p/
ቴሌግራም http://t.me/mowieethiopia
ዌብሳይት http://mowe.gov.et
X/ትዊተር https://x.com/mowe_ethiopia
ዩቱዩብ https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s
ቲክቶክ tiktok.com/@mowetikto