ለዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ የውሃ መረጃ አንባቢዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ
ለዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ የውሃ መረጃ አንባቢዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ
ነሐሴ 2/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) አዳማ ድሬ ኢንተርናሽናል ሆቴል
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የገጸ ምድር ውሃ ዴስክ ከቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት ጋር በጋራና በፕሮጀክቱ ድጋፍ ለዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ ጽ/ቤት የውሃ መረጃ አንባቢዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ።
የፕሮጀክት አስተባባሪው አቶ ሞላ ረዳ እንደገለጹት፣ የስልጠናው ዋና ትኩረት የውሃ ደረጃ፣ የዝናብ መጠንና ሌሎች የሀይድሮሎጂ መረጃዎችን በተወሰነው መስፈርት በትክክል መሰብሰብ፣ መመዝገብና በወቅቱ ማስተላለፍ የሚያስችል ነው።
እንዲሁም በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ የሚሰበሰቡ የሀይድሮሎጂ መረጃዎች በትክክል፣ በታማኝነትና በወቅቱ እንዲሰበሰቡ፣ እንዲመዘገቡና ለሚመለከተው አካል እንዲተላለፉ የውሃ መረጃ አንባቢዎችን የሙያ አቅም ለማጎልበት ያለመ መሆኑም ተገልጿል።
በስልጠናው የሀይድሮሎጂ መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳቦች፣ የውሃ መረጃ አንባቢዎች ሚናና ኃላፊነት፣ የውሃ ደረጃና የዝናብ መጠን አነባበብ፣ የመረጃ ምዝገባና ሪፖርት አቀራረብ፣ የመረጃ ጥራት ቁጥጥር፣ እንዲሁም የመለኪያ ጣቢያዎችና መሣሪያዎች አያያዝና ጥገና በንድፈ ሐሳብና በተግባር ተሰጠ።
በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ የሚሰበሰበው የሀይድሮሎጂ መረጃ ለውሃ ሀብት ዕቅድና አስተዳደር፣ ለጎርፍ ትንበያና ማስጠንቀቂያ፣ ለመስኖ ልማት፣ ለውሃ አቅርቦትና ለሌሎች የውሃ ሀብት ልማት ሥራዎች ወሳኝ ግብዓት በመሆኑ ትክክለኛ፣ የታመነ፣ የተሟላና ወቅታዊ መረጃ መኖሩ በተፋሰሱ የሚከናወኑ የውሃ ሀብት ዕቅድ፣ ልማትና አስተዳደር ሥራዎችን በተሻለ መረጃ ለመደገፍ እንደሚያስችል ተገልጿል።
በዚሁ ስልጠና፣ የውሃ መረጃ አሰባሰብና አያያዝ ሥርዓትን በማጠናከር ለዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ ዘላቂ የውሃ ሀብት ልማትና አስተዳደር የሚያስፈልገውን ታማኝ የመረጃ መሠረት ለማጠናከር የሚያስችሉ ሌሎች አጀንዳዎች ተካተውበት ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ይሆናል።
ከስልጠናው በኋላም ተሳታፊዎች በሞጆ አካባቢ የሚገኙ የሀይድሮሎጂ ጣቢያዎችን በመጎብኘት የመስክ ልምድ እንደሚያገኙና የመለኪያ ጣቢያዎችን አሠራር በተግባር እንደሚመለከቱ ተገልጿል።
ፌስቡክ
https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p/
ቴሌግራም
http://t.me/mowieethiopia
ዌብሳይት
http://mowe.gov.et
X/ትዊተር
https://x.com/mowe_ethiopia
ዩቱዩብ
https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s
ቲክቶክ
tiktok.com/@mowetikto