በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ባለፉት አምስት ዓመታት ጉልህ ውጤቶች ተመዝግበዋል

በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ባለፉት አምስት ዓመታት ጉልህ ውጤቶች ተመዝግበዋል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ.) – በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ጉልህና ተጨባጭ ውጤቶችን እንዳስመዘገቡ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በተካሄደው የአምስት ዓመት የዘርፉ የአፈጻጸም ማጠቃለያና የእውቅና መርሃ ግብር ላይ እንደገለጹት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት 75.59 በመቶ ደርሶ ከ84.4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሆነዋል። በተጨማሪም በከርሰ ምድር ውሃ ልማት 87.5 በመቶ አፈጻጸም መመዝገቡ ዘርፉ ያሳየውን እመርታ ያረጋግጣል ብለዋል።

በኢነርጂ ዘርፍም የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጨምሮ በርካታ ትላልቅ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በመጠናቀቅና ወደ ሥራ በመግባት የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም በማሳደግ ለኢኮኖሚ እድገትና ለማህበራዊ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ለተመዘገቡት ስኬቶች አስተዋጽኦ ላበረከቱ የመንግሥት ተቋማት፣ የልማት አጋሮች፣ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እውቅናና ምስጋና ተሰጥቷል። በቀጣይም የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ልማትን ይበልጥ ለማፋጠን የተጠናከረ ትብብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

በመርሃ ግብሩ የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች፣ የቀድሞ ሚኒስትሮች፣ የልማት ድርጅቶች ተወካዮች፣ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎች እንዲሁም የዘርፉ አመራሮችና ሠራተኞች ተገኝተዋል።

በዕለቱ የተደረገው ጉብኝት ውስጥ ለውሃ ሀብት አስተዳደር መሠረት የሆነውን የአገሪቱን የውሃ መረጃ አያያዝ በዘመናዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚያጠናክር የETH-BIS (Ethiopian Water Resources Information System) ሥርዓት በይፋ ተመርቆ ሥራ ጀምሯል። ሥርዓቱ የውሃ ሀብትን በመጠን፣ በጥራትና በስርጭት መረጃ መሰብሰብ፣ ማቀናጀት፣ ማቀድ፣ መመደብና በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ለመስጠት አስፈላጊ የሆነ ዘመናዊ መረጃ ሥርዓት መሆኑ ተገልጿል።

Share this Post