የተፋሰስ ምክር ቤት ረቂቅ ደንብ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተካሄደ።

የተፋሰስ ምክር ቤት ረቂቅ ደንብ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተካሄደ።

ሀምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም(.ው.ኢ.ሚ) የውሃ ሀብትን በተቀናጀ መንገድ ለማልማት፣ ለማስተዳደርና በቀጣይነት ለመጠቀም የሚያስችለውን የተፋሰስ ምክር ቤት ረቂቅ ደንብ ለማዳበር ያለመ የምክክር መድረክ ዛሬ በቢሾፍቱ ፒራሚድ ሆቴል ከፌዴራልና ከክልል ተቋማትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተካሂዷል።

መድረኩን የከፈቱት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ እንደገለጹት፣ በክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የሚመራው የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት አዋጅ ከጸደቀ በኋላ የአዋጁን ድንጋጌዎች በተግባር ለማዋል የተፋሰሶች ምክር ቤቶች አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባርን በዝርዝር የሚያስቀምጠው ረቂቅ ደንብ በባለድርሻ አካላት ሰፊ ተሳትፎ እንዲዳብር ይህ የምክክር መድረክ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም፣ ውሃ የሁሉም የጋራ ሀብት በመሆኑ በሳይንሳዊ መሠረትና በተቀናጀ አስተዳደር ሲመራ ለልማት፣ ለምግብ ዋስትና፣ ለኢነርጂ ምርት፣ ለኢንዱስትሪና ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ገልጸው፣ የረቂቅ ደንቡ ጥራት በባለድርሻ አካላት በሚቀርቡ ገንቢ ሀሳቦችና አስተያየቶች እንደሚጠናከር አስረድተዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ አዋጁ የውሃ ሀብትን ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋና ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ከማስቻሉም በላይ ከአየር ንብረት ለውጥ የሚመነጩ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም፣ የጎርፍና የድርቅ አደጋዎችን ለመቀነስ እና የውሃ ሀብት አስተዳደርን በተቀናጀ ሁኔታ ለማጠናከር ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት አዋጁ በዋናነት በአራት ዐበይት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ እነዚህም የተፋሰስ ዕቅድ ዝግጅትና ትግበራ፣ የተፋሰስ መረጃ ሥርዓት ማቋቋም፣ የውሃ ሀብት ምደባና አጠቃቀምን በፍትሃዊነት መምራት፣ እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ቅንጅትን ማጠናከር ናቸው።

የተፋሰስ ምክር ቤቶች በሀገሪቱ የውሃ ሀብት አስተዳደርን በማጠናከር፣ ተቋማዊ ቅንጅትን በማሳደግና ዘላቂ ልማትን በማፋጠን ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል።

በመድረኩ ላይ የረቂቅ ደንቡ ዝርዝር ይዘት በባለሙያዎች የቀረበ ሲሆን ተሳታፊዎች በምክር ቤቶቹ አደረጃጀት፣ በአባላት ውክልና፣ በተጠያቂነት፣ በቅንጅት ሥርዓት፣ በውሳኔ አሰጣጥ እና በአፈጻጸም ክትትል ዙሪያ ገንቢ አስተያየቶችን እንደሚያነሱ ይጠበቃል።

Share this Post