የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመታዊ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ግምገማ እያካሄደ ነው።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመታዊ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ግምገማ እያካሄደ ነው።

ሐምሌ 13/2018 ዓ.ም. (ው.ሚ.ኢ)

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በ2018 የበጀት ዓመት በመላ ሀገሪቱ እየተተገበሩ ያሉ ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ለመገምገም የተዘጋጀውን አመታዊ የፕሮጀክት ግምገማ መድረክ እያካሄደ ነው።

የግምገማ መድረኩ ክቡር ሚኒስቴሩ ፣ የፕሮጀክት አስተባባሪዎች ፣መካከለኛ አመራሮች፣ ኮንትራክተሮች አማካሪዎች አና ባለሙያዎች በተገኙበት እየተካሄደ ሲሆን፣ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ፣ በኢነርጂ ልማት ዘርፍ እና በውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ የተመዘገበውን አፈጻጸም በዝርዝር በመገምገም የተገኙ ውጤቶችን እና ያሉ ተግዳሮቶችን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ ነው።

በግምገማው የፕሮጀክቶች ፊዚካል እና ፋይናሻል አፈጻጸም በተለይ ትኩረት እንደተሰጠው ተገልጿል።

ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ፣ የበጀት አጠቃቀም፣ የሥራ ጥራት፣ የአፈጻጸም ፍጥነት እና የተገኙ ውጤቶች አንጻር በጥልቀት እየተገመገሙ ነው።

በመክፈቻው ንግግር እንደተገለጸው፣ ዛሬ የሁለተኛ ከተሞች የሳኒቴሽን ፕሮጅክቶች (2nd urban project) ግምገማ እየተካሄደ ሲሆን፣ በቀጣዮቹ ሦስት ቀናትም ተጨማሪ ፕሮጀክቶች በተመሳሳይ መልኩ ተገምግመው ውጤታቸው እንደሚቀርብ ተጠቁሟል።

የግምገማው ዋና ዓላማ የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በትክክል በመለካት የተመዘገቡ ስኬቶችን ማጠናከር፣ የተስተዋሉ እንቅፋቶችን መለየት፣ የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ እና በቀጣይ ዓመታት የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች በተሻለ ውጤታማነት እንዲፈጸሙ መሠረት መጣል መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም የፕሮጀክቶች ክትትልና ግምገማ ሥርዓትን በማጠናከር፣ የሀብት አጠቃቀምን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ፣ የተቋማዊ ተጠያቂነትንና ግልጽነትን ለማሳደግ የመድረኩ አስፈላጊነት ተጠቅሷል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በሳኒቴሽን መሠረተ ልማት ዝርጋታ ፣ በኢነርጂ ልማት እና በውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፎች እየተተገበሩ ያሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እና በተፈለገው ጥራት እንዲጠናቀቁ የክትትልና የግምገማ ሥራዎችን በቀጣይነት እንደሚያጠናክር ተገልጿል።

Share this Post