በአርባ ምንጭ ኩልፎ ወንዝ የሚከናወነው የአስቸኳይ ጊዜ የወንዝ ደለል ማስወገጃ ሥራ በተፋጠነ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ ተሰጠ።

በአርባ ምንጭ ኩልፎ ወንዝ የሚከናወነው የአስቸኳይ ጊዜ የወንዝ ደለል ማስወገጃ ሥራ በተፋጠነ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ ተሰጠ።

ሐምሌ 03/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ.)

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ የተመራ ቡድን፣ የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት አስተባባሪና የአርባ ምንጭ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች በአርባ ምንጭ ከተማ በኩልፎ ወንዝ እየተከናወነ ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ የወንዝ ደለል ክምችት ማስወገጃ ሥራ የመስክ ምልከታ አካሂዷል።

የመስክ ምልከታው በዓለም ባንክ ድጋፍ በሚተገበረው የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት አማካኝነት ባለፈው በኩልፎ ወንዝ የተከሰተውን ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ተከትሎ እየተከናወነ ያለውን የወንዝ ደለል ማስወገጃ ሥራ አፈጻጸም ለመገምገም፣ ያለበትን ደረጃ ለማየትና ቀጣይ የአፈጻጸም አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የተደረገ ነው።

በምልከታው ወቅት የፕሮጀክቱ አማካሪዎች ስለ ሥራው አጠቃላይ ሂደት፣ እስካሁን የተከናወኑ ሥራዎች እና ቀሪ ሥራዎች ዝርዝር ገለጻ ያቀረቡ ሲሆን፣ ተሳታፊዎቹም በመስክ በመገኘት የሥራውን አፈጻጸም ተመልክተዋል።

በዚሁ ወቅት ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ሥራው የበርካታ አካላት የጋራ ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸው፣ በተጀመረው ፍጥነት በመቀጠል በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አሳስበዋል።

በተለይም ከአካባቢ ተጽዕኖ፣ የደለል ማስወገጃ ቦታ ዝግጅት፣ የነዳጅ አቅርቦት እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ቀድመው እንዲፈቱ መመሪያ ሰጥተዋል።

በተጨማሪም አማካሪውና ኮንትራክተሩ በቅርበት በመቀናጀት እንዲሠሩ፣ እንዲሁም ከማኅበራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በሚኒስቴሩና በከተማ አስተዳደሩ በጋራ በአፋጣኝ እንዲፈቱ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ተመስገን ከተማ በበኩላቸው፣ ሥራው የአስቸኳይ ጊዜ ጣልቃ ገብነት እንደመሆኑ፣ የክረምት ዝናብ ተጠናክሮ ከመቀጠሉ በፊት ቀሪ ሥራዎችን በፍጥነት ማጠናቀቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የአርባ ምንጭ ከተማ መዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዳሙ በበኩላቸው፣ ባለፈው የተከሰተው ጎርፍ ከከፍተኛ የዝናብ መጠን በተጨማሪ በአካባቢው ያሉ የመሠረተ ልማት ተጽዕኖዎችም አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ገልጸው፣ ቀደም ሲል የተሠሩ የጎርፍ መከላከል ሥራዎች የአደጋውን መጠን በእጅጉ ለመቀነስ አስችለዋል ብለዋል።

በተጨማሪም የተጀመሩትን ሥራዎች ለማጠናቀቅ የከተማ አስተዳደሩ ሙሉ ትብብር እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ከመስክ ምልከታው በኋላ ቡድኑ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት እየተከናወነ ያለውን የሀይድሮሎጂ መረጃ አሰባሰብ እና የሀይቆች የውሃ ጥልቀት ልኬት (Bathymetry) ሥራ አፈጻጸም ላይ ውይይት በማድረግ ጉብኝቱን አጠናቋል።

Share this Post