በቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት በማይክሮሶፍት ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት በመታገዝ የሚገነባው አቅም ለተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ውጤታማነት!
በቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት በማይክሮሶፍት ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት በመታገዝ የሚገነባው አቅም ለተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ውጤታማነት!
አዳማ፣ሰኔ 26/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጅ ሚኒስቴር የሚተገበረው የቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት (BaSRINET) በማይክሮሶፍት የተቃኘ ዘመናዊ አሰራርን በዘርፉ ለመተግበርና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና በአዳማ ከተማ ሂል ሳይድ ሆቴል አዘጋጅቷል።
በአቅም ግንባታ ስልጠና መርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሃብት አጠቃቀምና ፈቃድ ዴስክ ኃላፊ አቶ ጨመዳ ቶሊ የቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት በአዋሽና በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ ለሚተገበረው የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ትልቅ ግብዓት እያበረከተ ያለ ፕሮጀክት መሆኑን የገለጹ ሲሆን የዕለቱ የአቅም ግንባታ ስልጠና በማይክሮሶፍት የዘመነ የአሰራር ስርዓት ላይ ተመስርቶ መሰጠቱም በእጅጉ አስፈላጊና ወቅቱን የዋጀ ስለሆነ ተሳታፊዎች ያገኙትን ግንዛቤ ወደ ተግባር በመቀየር ለዘርፉ እድገት የበኩላቸውን አሻራ ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ (BaSRINET) ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሞላ ረዳ በበኩላቸው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚተገበሩትን የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፣የኢነርጂ ልማትና የውሃ ሃብት አስተዳደር ዘርፎችን ለማሳለጥ ከተቀመጡት የ2030 አጀንዳ የሆኑ 17 ግቦችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ባዘርኔት ፕሮጀክት በሁሉም ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግና በማቀድ ለውጤታማነቱ መሳካት ሚናውን እየተወጣ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመሆኑም በጣሊያን መንግስት እየተደገፈ በአዋሽና ዋቢ ሸበሌ ተፋሰሶች ላይ የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት በዋናነት አምስት ዓላማዎችን ያነገበ ሲሆን እነዚህም የመረጃ ተደራሽነትን ማሻሻል ፣የውሃ ተደራሽነትን ማሳደግ፣የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ በማልማት እንዲያገግሙ ማድረግ፣የተቋማትን አቅም ማሳደግና እንዲሁም የኢነርጅ ተደራሽነትን ማስፋፋት መሆናቸውን አቶ ሞላ አብራርተዋል።
የዕለቱ የአቅም ግንባታ ስልጠና ዓበይት ዓላማዎችም የማይክሮሶፍት ፕሮጀክትን (ms-project) ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠቀም በፕሮጀክት አስተዳደር ተግባራት ዕቅድ ለማዘጋጀት፣ተግባራትን በተገቢ ሁናቴ ለመፈጸም የሚያስችል የጊዜ ሰሌዳ ለመቅረጽ ፣ ፍትሃዊ የሀብት ምደባ ለማድረግ ፣የአፈፃፀም ሂደትና ክትትል ለማካሄድና ሪፖርትን በአግባቡ ለማደራጀት አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥር ሲሆን የአስተግባሪዎችን ቴክኒካዊ እና ተግባራዊ አቅም ለማጠናከርም ብርቱ እገዛ ያደርጋል ተብሏል።
የስልጠናው አጀንዳ ሲቀረጽም በፕሮጀክት ማኔጅመንት ውስጥ ያለውን የአፈፃፀም ችግር እንዲፈታና የማስፈጸም አቅምን እንዲያሳድግ ና በተቋም ደረጃ ያለውን የፕሮጀክት ዕቅድና የአመራር ስርዓት እንዲያሻሽል ሆኖ በመዘጋጀቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ ተብራርቷል ።
የስልጠናውን ይዘት ለሰልጣኞች ያስተላለፉት ዶ/ር አለልኝ ዘሩ የብሉ ዲል የአዋሽ ፓርትነርሺፕ ፕሮግራም የተፋሰስ ኢንፎርሜሽን መረጃ አስተዳደር ፕሮጀክት ማናጀር ሲሆኑ የፕሮጀክት ዕቅድ ዝግጅት ፣ጽንሰ ሃሳብ፣በዕቅዱ መካተት ያለባቸው አይቀሬ መሠረታዊ ጉዳዮችን እና ሌሎች ተያያዥ አጀንዳዎችን በገለጻ ሲያቀርቡ ውለዋል።
መድረኩ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ አጀንዳዎች እየተላለፈ የሚቆይ ሲሆን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከስራቸው ጋር በቀጥታ ተዛምዶ ባለው መንገድ የሚመለከታቸው የስራ ክፍል ስራ አስፈጻሚዎች፣ ባለሙያዎችና ዴስክ ኃላፊዎች፣የፕሮጀክት አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች፣እንዲሁም ከተፋሰስ ጽ/ቤቶች የተጋበዙ የዘርፉ አስተግባሪዎች እየተሳተፉበት ሲሆን በቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት በማይክሮሶፍት ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት የሚገነባው አቅም ለተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በአብዛኞቹ ተሳታፊዎች እየተገለጸ ነው።