የኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውሃ ጥናት እና የውሃ ጉዶጓድ ቁፋሮና ግንባታ መመሪያዎች ለባለድርሻ አካላት ቀርበው ግምገማ ተካሄደባቸው።

የኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውሃ ጥናት እና የውሃ ጉዶጓድ ቁፋሮና ግንባታ መመሪያዎች ለባለድርሻ አካላት ቀርበው ግምገማ ተካሄደባቸው።

ሰኔ፣22/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ)

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የውሃና መሬት ሃብት ማዕከል በጋራ የሚተገብሩት የብራይት (BRIGHT)ፕሮጀክት የኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውሃ ጥናት እንዲሁም የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮና ግንባታ መመሪያዎች ላይ ግምገማ ለማካሄድ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በካፒታል ሆቴል ውይይት ሲያካሂድ ውሏል።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ አስቀድመው በከርሰ ምድር የውሃ ሃብት ዘርፍ በስራ ላይ የቆዩ፣ሲሰሩ የነበሩና አሁንም ስራውን በመምራት ላይ የሚገኙት ሙያተኞች እስከአሁን ላበረከቱት አስተዋፅኦ አመስግነው ይህ ተግባርም አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ያለ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በአጽንኦት አሳስበዋል።

ከዚህ ቀደም በዘርፉ ከተስተዋሉ ልምዶች በመነሳትም በከተሞች የከርሰ ምድር ውሃ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀነስ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑ፣በዘርፉ የሚሰማሩ ሙያተኞች ስብጥር ግልጽ መስፈርት ማስቀመጥ ትኩረት የሚሰጠው ስለመሆኑ፣በአማካሪና በኮንስትራክሽን ካምፓኒ መካከል ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮችን አስቀድሞ ማስወገድ ፣ በተገልጋዮች ዘንድ የሚነሱ ቅሬታዎችን መፍታት ትኩረት የሚሰጠው መሆኑ እንዲሁም የመረጃ አያያዝን ማደራጀትና ማዘመን ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንና ሌሎች ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮችን ክቡር ሚኒስትሩ አውስተው በተለይም በሃገሪቱ በዘርፉ ለሚገጥመው ስኬትና ውድቀት ተጠያቂነት ሊኖር እንደሚገባና ለዚህም አስቀድሞ የተግባር ዕቅድ በአግባቡ ማዘጋጀትና መፈተሽ ለዘርፉ ትልቅ ውጤት ያስመዘግባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘም እነዚህ የተጠቀሱት መሠረታዊ ጉዳዮች በተመረጡ የኮሚቴ አባላት በደንብ ተቃኝተው በተዘጋጀው መመሪያ መካተት የሚችሉበትን ሁኔታ ማጤን ይገባል ብለዋል።

የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ጠና አላምረው ለተሳታፊዎቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ካስተላልፉ በኋላ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል በከርሰ ምድርና በገጸ ምድር ውሃ ልማት ዙሪያ የሚሰሯቸውን በርካታ ስራዎች ጠቅሰው ይህንንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የብራይት ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ማማሩ አያሌው በበኩላቸው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል እ.ኤ.አ በ2023 ወደ ስራ ሲገቡ በብራይት (BRIHT) ፕሮጀክት አማካኝነት ሊሰሩ ታቀዱ ተግባራት በዋናነት የተቋማት አቅምን መገንባት፣ የውሃ ሀብት የተፋሰስ መረጃን ማደራጀት፣የተፋሰስ ዕቅድ ዝግጅትና የተቀናጀ የውሃ ሀብት ለማስተዳደር የሚያስችል መመሪያና ደንብ ማዘጋጀት እንደነበሩ አስታውሰዋል።

የዕለቱ መርሐ ግብር ዋና ዓላማም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ከርሰ ምድር ውሃ ጥናት መመሪያና በከርሰ ምድር ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮና ልማት ዙሪያ ሁለት መሠረታዊ መመሪያዎች መዘጋጀታቸውንና ይህንን መመሪያ ተመርኩዞ ወደ ተግባር ለመግባት ለአጋር አካላት ማስገንዘብና ማስገምገም አስፈላጊ በመሆኑ መድረኩን መፍጠር አስፈልጓል ብለዋል።

በመመሪያ ዝግጅቱ የነበረውን ሂደት አስመልክቶም ዶ/ር ማማሩ ሲያብራሩ የከርሰ ምድር ውሃን በአግባቡ በመያዝ ዘላቂ በሆነ መንገድ ለማስተዳደር እንዲቻል ከስድስት ወራት በፊት ከክልል ፣ከተፋሰሱ ጽ/ቤቶች፣ ከአማካሪዎች፣ ከውሃና ኢነርጅ ሚኒስቴርና ከውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ኃላፊዎችና ባለሙያዎችን ያሳተፈ ቴክኒካል ቡድን በማቋቋም ወደ ስራ መገባቱንና መመሪያዎቹ በተለያየ ጊዜ ማስተካከያ እየተደረገባቸው ለዛሬው መድረክ መብቃታቸውን አስረድተዋል።

በመድረኩ የመመሪያው ቅድመ ዝግጅት ፣የኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ጥናትና የከርሰ ምድር ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ግንባታ መመሪያዎች ይዘት፣የቴክኒክ ቡድኑ ሚና፣ የባለድርሻ አካላት ግብረ መልስ፣እንዲሁም የሚጠበቁ ውጤቶችና ሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች በገለጻ ቀርበዋል።

የቀረቡ መመሪያዎችን ተከትሎ ተሳታፊዎቹ በርከት ያሉ አስተያየቶችን የሰነዘሩ ሲሆን አብዛኞቹ በመመሪያዎቹ ዙሪያ በግብዓትነት የተነሱት ሃሳቦች ሚዛን የሚደፉ ሆነው ተገኝተዋል ተብሏል ።

መድረኩን ያወያዩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳና ዶ/ር ጠና አላምረው ሲሆኑ ክቡር አቶ ሞቱማ በዘርፉ መመሪያ አለመዘጋጀቱ አሳሳቢ የነበረ ጉዳይ ሲሆን አሁን መዘጋጀቱ ደግሞ አስገዳጅ መሆኑን መገንዘብ አለብን ያሉ ሲሆን ይህ የሆነበት ምክንያትም

በአሁኑ ወቅት ለመጠጥ ውሃ ፣ለኢንዱስትሪና ለግብርና ግልጋሎት እየተጠቀምን ያለነው የከርሰ ምድር ውሃን ስለሆነ ነው ብለዋል።

በመጨረሻም በባለድርሻ አካላት በተነሱ አስተያየቶችና ማብራሪያ በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የስራው ባለቤቶች ተጋብዘው ምላሽ የሰጡ ሲሆን የተነሱ ሃሳቦች በኮሚቴው እንዲታዩና አስፈላጊ ሆነው ሲገኙ በማካተት መመሪያው በጊዜ ወደ ተግባር እንዲገባበት በማሳሰብ የዕለቱ መርሃ ግብር ተጠናቋል።

Share this Post