የብቃት ምዘናው የሪፎርሙን ስኬት የሚያረጋግጥ ወሳኝ መሳሪያ ነው። ዶ/ር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ
የብቃት ምዘናው የሪፎርሙን ስኬት የሚያረጋግጥ ወሳኝ መሳሪያ ነው።
ዶ/ር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20/2018 ዓ.ም. (ውኢሚ)
ለውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ሰራተኞች በየብቃትና ምዘና ማዕቀፍ እና የብቃት ሥራ አመራር ይዘትና አተገባበር ላይ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቀቀ።
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ፣ የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ሰራተኞች ጠንካሮችና ብቁ በመሆናቸው የብቃት ምዘናውን በውጤታማነት እንደሚያጠናቅቁ ያላቸውን እምነት በመግለጽ ሰራተኞቹን አበረታተዋል።
ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ በሁለተኛው የሪፎርም ማዕበል ከሀምሌ 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሪፎርም ሂደት በመግባት ከ100 በላይ የሪፎርም ሰነዶችን አዘጋጅቷል።
እነዚህን ሪፎርሞች በተግባር የሚያስፈጽም ብቃት ያለው የሰው ኃይል መኖሩን ለማረጋገጥ የብቃት ምዘናው አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህ ሪፎርም ከዚህ ቀደም እንደነበረው የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ሳይሆን የተቋማችን ሪፎርም ነው። ስለዚህ የብቃት ምዘናውን ለሀገራችን፣ ለተቋማችን እና ለራሳችን የሚጠቅም አጋጣሚ አድርገን ልንወስደው ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።
ለብቃት ምዘናው በቂ ዝግጅት ማድረግ፣ በተደጋጋሚ መለማመድ እና በስነ ልቦና ጠንካራ መሆን እንደሚገባ ያሳሰቡት ሚኒስትሩ፣ ሰራተኞች ተቋሙንና ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የእድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር በሚደረገው ጉዞ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ሰራተኞች በማንኛውም ወሬ የሚረበሹ ሳይሆኑ ሌሎችን የሚያረጋጉና ስለ ብቃት ምዘናው ዓላማ ግንዛቤ የሚፈጥሩ እንደሆኑ ያላቸውን መተማመን ገልጸዋል።
እንደ ዘርፉ የሪፎርም አካልም የሰራተኞችን የሥራ አካባቢ ለማሻሻል የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸው፣ የሰራተኞች ካፌን ጨምሮ ቢሮዎችን፣ መቀመጫዎችን፣ መዝናኛ ስፍራዎችንና ሌሎች ለስራ ምቹ እና ማራኪ አካባቢዎችን የመፍጠር ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።