የከተማ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን አገልግሎት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ለማቋቋም በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ውይይት ተደረገ።

የከተማ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን አገልግሎት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ለማቋቋም በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።

አዳማ:-ሰኔ 05/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ አስተባባሪነት የከተማ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን አገልግሎት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ለማቋቋም በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።

የውይይት መድረኩን ያስጀመሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ የከተሞች የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን አገልግሎት ተቆጣጣሪ ባለስልጣንን ለማቋቋም እየተሰራ ያለውን ሂደት ለማሳወቅ፣ የሚቋቋመው የፌዴራል ተቆጣጣሪ ባለስልጣን አዋጅ ላይ ማብራሪያ ለመስጠት እንዲሁም ባለስልጣኑ ሊጠቀምባቸው በሚችለው መሠረታዊ የቁጥጥር መሣሪያዎች ላይ ስልጠናና ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል መድረክ ነው ብለዋል።

ተቆጣጣሪው ባለስልጣን የውሃውን አገልግሎት አሰጣጥ የሚሻሙ አካላቶችን ወደ ህግ ማዕቀፍ በማስገባት ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ አሰራር እንዲኖር ያስችላል ያሉት ክቡር አምባሳደር የውሃ ሀብታችንም ያለአግባብ እንዳይባክን ያግዛል ብለዋል።

ክቡር አምባሳደር አክለውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ በቀጣይ ከሚሰሩ በርካታ ስራዎች መካከል ከውሃ በሚገኘው ገቢ የሀገራችንን ኢኮኖሚ ማሻሻል እንደሚገባ ጠቁመው፤ በአማካሪዎች የሚቀርበውን ሰነድ በማዳበር ለሚመለከተው አካል ማቅረብና ወደ ትግበራ እንዲገባ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ክቡር አምባሳደር ለአዋጁ ዝግጅት አስተዋፅኦ ያደረኩ አካላትን ጨምሮ የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉትን የአለም ባንክንና ዩኒሴፍን አመስግነዋል።

እንደተቋም አገር አቀፍና ገለልተኛ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ለማቋቋም በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲሰሩ እንደነበር የጠቆሙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃ ተቋማት ክትትልና ድጋፍ ዴስክ ኃላፊ አቶ ኃይማኖት በለጠ ሰነዱን በውይይት ከማዳበር ጀምሮ ተቋማዊ የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ከፍትህ ሚኒስቴር እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር ውይይት እንደተደረገበትም አስታውሰዋል።

አዋጁ በዋናነት ፍቃድ አሰጣጥ እና ተገዢነት /Licensing & Compliance/ አንደኛው ሲሆን ለአገልግሎት ሰጪዎች የሚወጡ መስፈርቶች፣ የንብረት አስተዳደር፣ ያልተመዘገበ ወይም የሚባክን ውሃ እና የውሃ ጥራት ቁጥጥር ላይ ያለመ፤ ሁለተኛው ደንበኛ ተኮር መሣሪያዎች /Customer-Centered Tools/ ሲሆን የደንበኞችን ጥቅም ማስጠበቅ፣ የደንበኞች ቻርተር ተገዢነት እና የውሃ ቆጣሪ ደንቦች ላይ የሚያተኩር እንዲሁም ሶስተኛው አፈፃፀም እና መልካም አስተዳደር /Performance and Governance/ የብሔራዊ አፈፃፀም መለኪያ መመሪያዎች እና የቦርድ አባላት እንዲሁም የዋና ሥራ አስፈፃሚዎች የሥነ-ምግባር ደንብን ያካተተ ነው።

ተቆጣጣሪ ባለስልጣኑን ለማቋቋም የሚያስችሉ ሰነዶች በግለሰብ አማካሪዎች /Individual Consultant/ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።

በመድረኩ የክልሎች የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የከተሞች ውሃና ፍሻሽ አገልግሎት ድርጅት ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ ከተሞች መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽ ፌዴሬሽን የስራ ኃላፊዎች፣ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚመለከታቸው ስራ አስፈፃሚዎችና ባለሞያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው ባለሞያዎች እየተሳተፉ ሲሆን መድረኩ ለተከታታይ ሶስት ቀናት ይቀጥላል።

Share this Post