የቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት ዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ በንግድና ስራ ፈጠራ ዙሪያ ለሴቶች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ ነው።

የቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት ዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ በንግድና ስራ ፈጠራ ዙሪያ ለሴቶች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ ነው።

ጎዴ፣ሰኔ 5/2018 ዓ.ም.በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት /BaSRINET project/ በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ በንግድና ስራ ፈጠራ ዙሪያ በሸበሌ ሆቴል ለሴቶች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ ነው።

በስልጠናው እየተሳተፉ የሚገኙት ከጎዴ ከተማ ቀላፎ ወረዳ የማህበረሰብ ክፍል የተመረጡ ሴቶች ናቸው።

በመድረኩ ላይ ተጋብዘው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሸበሌ ዞን ምክትል አስተዳደር አቶ ኢሴ አብዱላሂ

በራኪ በበኩላቸው የቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት የተለያዩ የልማት ስራዎችን በዘላቂነት ለመፍታትና በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሃብት የሚያጎለብቱና የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው የተዘጋጀውን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወደ ተግባር እንዲለውጡ አደራ ብለዋል።

በዕለቱ መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ /BaSRINET/ፕሮጀክት የክትትልና ግምገማ ባለሙያ አቶ ብርሀኑ መኮንን በመርሃ ግብሩ ላይ የፕሮጀክቱን ሁኔታ ከአቅም ግንባታ ስልጠና ጋር በማገናኘት ገለፃ ያደረጉ ሲሆን የቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት የማህበረሰቡን በርካታ ችግሮች ዘላቂ በሆነ መንገድ የሚፈታ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሆኑንና ሁለት ትላልቅ ወንዞችን ተከትሎ በአዋሽ እና በዋቢ ሸበሌ ተፋሰሶች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

አክለውም የዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ በኦሮሚያና በሶማሊ ክልሎች እንደሚተገበር ተናግረዋል።

በተጨማሪም ፕሮጀክቱ የውሃ እጥረት ያለባቸውን አካባቢዎች ችግር በማጥናት የውሃ አቅርቦትን ለማሳለጥ ለሰው ልጆች ፣ለእንስሳት እንዲሁም ለመስኖ ዓላማ ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚሰራ፣የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ የሚሰሩ ስራዎች እንዳሉ፣በተወሰነ መልኩም ቢሆን የሶላር አቅርቦት ላይም ድጋፍ እንደሚያደርግ እንዲሁም ልዩ ልዩ አቅምን የማጎልበቻና የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በዕለቱም ሴቶች በስልጠናው ከሚያገኙት ግንዛቤ በመነሳት ገቢያቸውን እንዲያጠናክሩና ራሳቸውን እንዲያሻሽሉ በአጽንዖት አሳስበዋል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ባለሙያ ወ/ሮ ሀረገወይን አሰፋ በበኩላቸው የተሰጣችሁን ዕድል በመጠቀም የተመረጣችሁ ሴቶች እንችላለን የሚለውን መፈከር በመሰነቅ ተለውጣችሁ እንድትገኙና ሌሎች ድጋፍ ለሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች እገዛ በማድረግ ውጤታማ እንድትሆኑ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ይፈልጋል ሲሉ ለተሳታፊዎቹ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ስልጠናው የሴቶችን አቅም ሊገነቡ በሚችሉ የተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ የተዘጋጀ ሲሆን ከትናንትናው ዕለት ጀምሮ ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ይገኛል።

Share this Post