የህዳሴ ግድብና የቀይ ባህር ዲፕሎማሲ፡ የኢትዮጵያ አዲስ ጂኦፖለቲካዊ ምዕራፍ

የህዳሴ ግድብና የቀይ ባህር ዲፕሎማሲ፡ የኢትዮጵያ አዲስ ጂኦፖለቲካዊ ምዕራፍ

በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአገራት ኃይል የሚለካው በወታደራዊ አቅም ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ፣ የኢነርጂ፣ የውሃ እና የጂኦፖለቲካ ተጽዕኖ በመፍጠር ጭምር ነው።

በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ በሁለት ታላላቅ ብሔራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የተለየ የዲፕሎማሲ ጉዞ አድርጋለች።

እነዚህም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና የቀይ ባህር ተደራሽነት ጉዳይ ናቸው።

ሁለቱም ጉዳዮች ከኢኮኖሚ ጥቅም ባሻገር የአገሪቱን የህልውና ጥያቄ፣ የቀጣናዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና የወደፊት የልማት አቅጣጫ የሚወስኑ ናቸው።

በእነዚህ መስኮች የተመዘገቡ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶችም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በምሥራቅ አፍሪካ እየተጠናከረ የመጣ የኃይል ማዕከል መሆኗን አመላክተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ትኩረት የሳበ ፕሮጀክት ነበር።

በተለይም የዓባይ ውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ በታሪክ የተፈጠሩ የፖለቲካ እና የጂኦፖለቲካ አለመግባባቶች ግድቡን ከቀላል የልማት ፕሮጀክት ወደ የዲፕሎማሲ ፈተና ቀይረውት ነበር።

ሆኖም ኢትዮጵያ “ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም” እንዲሁም “በሌሎች ላይ ጉልህ ጉዳት አለማድረስ” በሚሉ ዓለም አቀፍ መርሆዎች ላይ ተመስርታ የተከተለችው የዲፕሎማሲ መንገድ ትልቅ ውጤቶችን አስመዝግቧል።

ከተመዘገቡት ታላላቅ ድሎች አንዱ የግድቡ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ እንዲመራ ማድረግ ነው።

ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረኮች በመውሰድ ጫና ለመፍጠር የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን መፍትሔ ሊያገኙ ይገባል የሚለውን መርህ በተግባር አስከብራለች።

ይህ የዲፕሎማሲ ድል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ የተቋማዊ ነጻነት እና የአህጉራዊ ትብብር ማሳያ ሆኗል።

ሌላው ታላቅ ስኬት የግድቡ ግንባታ በውጭ ጫናዎች ሳይቆም እስከ መጨረሻው የውሃ ሙሌት መድረሱ ነው።

በሕዝብ ገንዘብና በብሔራዊ አንድነት የተገነባው ግድብ የኢትዮጵያን የራስ አቅም እና የውጭ ጫናን የመቋቋም ችሎታ አሳይቷል።

ዛሬ ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለአጎራባች አገራት ለሚደረገው የኃይል ሽያጭ መሠረት ሆኗል። ይህም ግድቡ የግጭት ምንጭ ሳይሆን የቀጣናዊ ትስስርና የጋራ ልማት መሣሪያ መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።

የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን ከተራ የኤሌክትሪክ አምራች ወደ የቀጣናው የኢነርጂ ማዕከል እየቀየራት ነው። ለጅቡቲ፣ ለኬንያ፣ ለሱዳን እና ለሌሎች አገራት የኃይል አቅርቦት መስፋፋቱ የኢኮኖሚ ትስስርን ከማጠናከሩም በላይ የፖለቲካ መተማመንን እየፈጠረ ነው።

ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያሳየች ያለች አገር ብትሆንም፣ የባሕር በር አልባ መሆኗ ለንግድ፣ ለኢኮኖሚ እና ለብሔራዊ ደኅንነት ከፍተኛ ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

በቅርብ ዓመታት ግን ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋን ከታሪካዊ ቅሬታ ወደ ስትራቴጂካዊ ዲፕሎማሲ ቀይራለች።

ከሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ (MoU) በዚህ ረገድ ታሪካዊ እርምጃ ተብሎ ይታያል። ይህ እርምጃ ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን በሰላማዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማሳካት ያላትን ቁርጠኝነት አሳይቷል።

ይህ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ኢትዮጵያ ከአንድ ወደብ ብቻ ጥገኛ የመሆን አደጋን ለመቀነስና የንግድ ወጪዋን ለመቆጣጠር የሚያስችል አዲስ የጂኦኢኮኖሚ አስተሳሰብ እንዳላት አሳይቷል።

ቀይ ባህር ከዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች አንዱ እንደመሆኑ መጠን በዚህ አካባቢ የሚፈጠሩ የደኅንነት ችግሮች በቀጥታ ኢትዮጵያን ይነካሉ።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ጉዳይ ተመልካች ሳይሆን ንቁ ባለድርሻ መሆን እንዳለባት በዲፕሎማሲ መድረኮች ላይ በግልጽ ማስቀመጥ ችላለች። ይህም የአገሪቱን የጂኦፖለቲካ ተጽዕኖ እያሳደገ ነው።

የህዳሴ ግድብና የቀይ ባህር ዲፕሎማሲ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ቢመስሉም፣ የጋራ ዓላማ አላቸው። ይህም ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ፣ በኢነርጂ እና በጂኦፖለቲካ የቀጣናው የኃይል ማዕከል ማድረግ ነው።

የህዳሴ ግድብ የኢነርጂ ተጽዕኖን ሲፈጥር፣ የቀይ ባህር ዲፕሎማሲ ደግሞ የንግድና የስትራቴጂካዊ ተደራሽነትን ያጠናክራል። ሁለቱም ተደጋጋፊ ሲሆኑ የኢትዮጵያን የወደፊት ኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ኃይል ለመገንባት ወሳኝ ሚና አላቸው።

በህዳሴ ግድብና በቀይ ባህር ጉዳዮች ዙሪያ የታዩት የዲፕሎማሲ ስኬቶች ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን በውይይት፣ በጽናት እና በስትራቴጂካዊ አመራር ማስከበር እንደምትችል አረጋግጠዋል።

ይሁን እንጂ እነዚህ ድሎች ዘላቂ ውጤት እንዲያመጡ የውስጥ አንድነትን ማጠናከር፣ ከጎረቤት አገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መገንባት እና የሰላም ዲፕሎማሲን ማስቀጠል አስፈላጊ ነው።

የህዳሴ ግድብ የኢነርጂ ነፃነትን ሲያመጣ፣ የቀይ ባህር ዲፕሎማሲ ደግሞ የኢትዮጵያን የጂኦፖለቲካ ተደራሽነት ያሰፋል። ሁለቱም ተደምረው ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ተጽዕኖ ፈጣሪ አገር ወደማድረግ እየመሯት ነው።

Share this Post