ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደርን በቢሯቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደርን በቢሯቸው ተቀብለው አነጋገሩ ።
ግንቦት 18/2018 ዓም (ው.ኢ.ሚ)በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደሩን ክቡር ሚሮስላቭ ኮሴክን በቢሯቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
በዕለቱ ሁለቱ ሃገራት በውሃ ሃብት አስተዳደር ዘርፎች በሚሰሯቸው የጋራ ስራዎች ዙሪያ የመከሩ ሲሆን በተለይም በሃገሪቱ የሃይድሮሎጂና ጂኦሎጂ ካርታ ዝግጅትና ይዘት ዙሪያ ሃሳብ ተለዋውጠዋል ።
ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ለክቡር አምባሳደሩ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ካደረጉ በኋላ ኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክ የረጂም ዓመታት ተጠናክሮ የቀጠለና ስር የሰደደ ታሪካዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስርና ትብብር የነበራቸው መሆናቸውን አስታውሰዋል።
አሁንም እነዚህ ሃገራት ከውሃና ኢነርጂ ዘርፉ ጋር በተገናኘ ከሃገሪቱ ሃይድሮሎጂና ጂኦሎጂ ጉዳዮች ጋር ግንኙነት ባላቸው ተግባራት በአብሮነትና በመደጋገፍ የሚሰሯቸው ስራዎች ዘርፈ ብዙ በመሆናቸው በዚህም መመስገን እንዳለባቸውና በቀጣይም ትብብሩ አዎንታዊ በሆነ መልኩ ዘላቂ እንዲሆን ክቡር አቶ ሞቱማ አሳስበዋል።
በዕለቱም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቼክ ፕሮጄክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሙሁዲን አብደላ በፕሮጀክቱ የተሰሩ ስራዎችን አፈጻጸም ያቀረቡ ሲሆን በዋናነት የሲዳማ፣ የጌዲኦና የጋሞን ሃይድሮሎጂና ጂኦሎጂካል ተግባራት በማስረዳት በእነዚህ አካባቢዎች 100ሺህ ስኬል መሰራቱንና በጠቅላላ የሃገሪቱን ሽፋንም 1ሚሊዮን ስኬል ማድረስ መቻሉን በሰነድ አስደግፈው አቅርበዋል።
በተጨማሪም የሃገሪቱን መሬት ማበልጸግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች፣በመረጃ ልውውጥ ሁኔታ ፣ በመሬት ልየታ ጉዳይ፣ በአቅም ግንባታ ስራዎችና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸውን ነጥቦች ያቀረቡ ሲሆን ኢትዮጵያ ያረፈችበትን የአለት ዓይነትና አለቶች የከርሰ ምድር ውሃ የመያዝ አቅማቸውን የሚያሳይ የሃይድሮሎጂና የጂኦሎጂ ካርታ በማብራራት በዝግጅቱ ወቅትም ከሁለቱ ሃገራት የተውጣጡ ሰላሳ ስምንት የዘርፉ ሙያተኞች የተሳተፉበት እንደነበር አስረድተዋል።
የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ክቡር ሚሮስላቭ ኮሴክ (H.Miroslav Kosek) በበኩላቸው ኢትዮጵያ የበርካታ ተፈጥሯዊ ሃብት ባለቤት በመሆኗ እንደሚወዷት ገልፀው በተለይም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በውሃ አስተዳደር ዘርፉ በጋራ በመሆን የሚሰሯቸው ስራዎች ሰፊ መሆናቸውን እና በመድረኩ ላይ በሃይድሮሎጂካልና ጂኦሎጂካል ተግባራትና ዝግጅት ላይ ተመርኩዞ በቀረበው የተሟላ ገለጻና ማብራሪያ ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ አመስግነዋል ።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል የተሳተፉት የዘርፉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችም የቼክ ሪፐብሊክ በቀጣይ የትምህርት ዕድል በማመቻቸት ረገድ፣በጥናትና ምርምር ስራዎች መደረግ ባለባቸው ድጋፎች ፣በውሃ ጥራትና በከርሰ ምድር ውሃ አጠቃቀምና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስተያየታቸውን ለግሰዋል።
የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደሩና የቡድን አባሎቻቸውም
የቼክ ሪፐብሊክ በውሃ አጠቃቀም ዘርፉ ጥሩ ተሞክሮ ያላት ሃገር በመሆኗ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር ግንኙነት ባላቸው ተግባራት ዙሪያ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ በአፅንኦት ተናግረው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዚህ ዘርፍ ከግል ካምፓኒዎች ጋር በጋራ ቢሰራ የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆን አስተያየታቸውን የለገሱ ሲሆን በተጨማሪም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኮንሴፕት ኖት በዝርዝር በማዘጋጀት በኢንባሲው በኩል እንዲያቀርብ የቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በመድረኩ ከውሃና ኢነርጂ የዘርፉ አማካሪ ፣ የክቡር ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ፣የከርሰ ምድር ውሃ ጥናትና ሞዴሊንግ ዴስክ ኃላፊ፣የቼክ ሪፐብሊክ የትብብር ሃላፊ ሚስ ባርቦራ ዛክ ቭላሶቫ እንዲሁም የኢኮኖሚና ንግድ ዘርፍ ትብብር ረዳት የሆኑት ቃልኪዳን አያሌው ተሳትፈውበታል።