የውሃ ሃብትን ለቀጣናዊ ትስስር ማጠናከሪያነት ማዋል እንደሚቻል የሕዳሴ ግድብ ማሳያ ነው
የውሃ ሃብትን ለቀጣናዊ ትስስር ማጠናከሪያነት ማዋል እንደሚቻል የሕዳሴ ግድብ ማሳያ ነው
ግንቦት 20/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአህጉሪቱን የውሃ ሀብት ለዜጎች ተጠቃሚነትና ለሀገራት የእርስ በርስ ትስስር ማጠናከሪያነት ማዋል እንደሚገባ ገለጸ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት 63ኛውን የአፍሪካ ቀን የሚዘክር ኮንፈረንስ ተካሂዷል።
ኮንፈረንሱ የአፍሪካ ኅብረት የ2026 ዓመታዊ መሪ ሃሳብ በሆነው "የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት ዘላቂ የውሃ ተደራሽነትን እና አስተማማኝ የንፅህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ" ላይ ያተኮረ ነበር።
በዚህም የውሃ ደህንነትን ማረጋገጥ፣ ለሁሉም ተደራሽ የሆነ የንፅህና አጠባበቅ ሥርዓት፣ የማህበረሰብ የመቋቋም አቅም፣ ሳይንስና ኢኖቬሽን፣ ፓን-አፍሪካኒዝም እና አንድነት እንዲሁም ዘላቂ መጻኢ እድል በሚሉ ስድስት ቁልፍ ምሰሶዎች ላይ በስፋት ተመክሯል።
ኢትዮጵያ በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ያላትን ግዙፍ ተሞክሮ ያጋራች ሲሆን፤ በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገሪቱን የውሃ ደህንነትና አረንጓዴ ኢነርጂ ፍላጎት ከመመለስ ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት የሚተርፍ የኃይል አቅርቦትና ቀጣናዊ ትስስርን በመፍጠር ረገድ እንደ ትልቅ ስኬት ቀርቧል።
ግድቡ የውሃ ሃብትን ለቀጣናዊ ትስስር ማጠናከሪያነት ማዋል እንደሚቻል ዓይነተኛ ማሳያ መሆኑ ተገልጿል።
የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን በጋራ በማስተባበር ረገድ ውጤታማ የሆነው "የተቀናጀ የውሃ፣ የንፅህና እና የጤና አጠባበቅ (One WASH National Program)" ተሞክሮዋ ለተሳታፊዎች ቀርቧል።
በመድረኩ ለፈጣን የከተሞች ዕድገትና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚታዩ የቴክኖሎጂና የፋይናንስ ክፍተቶችን በአጋርነት ለመፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ በመድረኩ እንዳሉት፤ የጋራ የውሃ ሀብቶችን ለጠንካራ የሃይድሮ-ዲፕሎማሲ ስራ መጠቀም ይገባል።
በአህጉሪቱ ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች በመኖራቸው የውሃ ሀብት አስተዳደር ቀጣናዊ ትብብር መጎልበት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሀገር ውስጥ የፋይናንስ አቅም መገንባቱን አስታውሰው፤ ግድቡ ለቀጣናዊ ትስስር አስተዋጽኦ በማድረግ ለአፍሪካ ሀገራት በምሳሌነት እንደሚጠቀስ አንስተዋል።
በመድረኩ የክልል የውሃ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።