የድህረ-ፕሮጀክት አፈጻጸም አስተዳደር ረቂቅ ጋይድ ላይን ላይ ውይይት ተደረገ።
አዳማ ፣ መስከረም 21/ 2019 ዓ.ም.
የፕሮጀክቶችን ርክክብ፣ ድህረ-ርክክብ ሥራዎችንና መዝጊያ ሂደቶችን በአንድ የተቀናጀ አሠራር ለመምራት፣ ተጠያቂነትንና የሥራ ጥራትን ለማጠናከር የተዘጋጀው የድህረ-ፕሮጀክት አፈጻጸም አስተዳደር ረቂቅ ጋይድ ላይን ላይ ውይይት ተደረገ።
ጋይድ ላይኑ ፕሮጀክቶች ከተጠናቀቁ በኋላ ያለው ሂደት በግልጽ አሠራር እንዲመራ ለማድረግ፣ ፕሮጀክቶች ለርክክብ ከመቅረባቸው በፊት ማሟላት የሚገባቸውን ለመወሰን፣ ከርክክብ በኋላ የሚቀሩ ሥራዎች በአግባቡ እንዲመሩ እና እንዲጠናቀቁ ለማስቻል እንዲሁም የፕሮጀክት መዝጊያ ሂደት በሰነድ የተደገፈና ተጠያቂነት ያለው እንዲሆን ያስችላል።
የጋይድ ላይኑን ገለጻ ያቀረቡት ዶ/ር አድማሱ ቴሶ ፕሮጀክቶች ከዕቅድ እስከ አፈጻጸም፣ ርክክብና መዝጊያ ድረስ በተደራጀ ሥርዓት እንዲመሩ የሚያግዝ፣ በተለይም ከፕሮጀክት ርክክብ በኋላ የሚከናወኑ ሥራዎችን በግልጽ ለመወሰንና በተገቢው አካል እንዲፈጸሙ ለማድረግ ያለውን ሚና አብራርተዋል።
በፕሮጀክት የመዝጊያ ሂደት የፕሮጀክቱን ዓላማ፣ የታቀደና የተገኘ ውጤት፣ የጊዜና የበጀት አፈጻጸም፣ የርክክብ ሁኔታ፣ የቀሩ ሥራዎች፣ የውልና የፋይናንስ ጉዳዮች፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የተገኙ ትምህርቶች እንደሚካተቱ አብራርተዋል።
በተጨማሪም የፋይናንስ ምንጭ፣ የወጪ አወቃቀር፣ የሥራ ማስኬጃና የጥገና ወጪዎች እንዲሁም የወጪ መመለሻ ሥርዓት በግልጽ መወሰናቸው የፕሮጀክቶችን ዘላቂነት ለማረጋገጥ እንደሚያግዝም ተገልጿል።
በቀረበው ሰነድ መነሻነት ጋይድ ላይኑ በተግባር የሚውልና የተቋሙን አሠራር የሚያሻሽል እንዲሆን ከግንዛቤ ፈጠራ፣ ከዲጂታል አሠራር፣ ከተጠያቂነትና ከተግባራዊነት አንጻር ሌሎችም ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችና አስተያየቶች ተነስተዋል።
ለተነሱት ሀሳቦች የማጠቃለያ ምላሽ የሰጡት የሰራ አመራር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኦልቀባ ባሼ፣ ረቂቅ መመሪያው ሲዘጋጅ በተቋሙ ውስጥ ያሉ ማኑዋሎችና አሠራሮች ተፈትሸው እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ተግባራዊ ሊሆን በሚችል መልኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
አቶ ኦልቀባ አክለውም፣ እንደዚህ ያሉ የውይይት መድረኮች የጋራ ግንዛቤን ለማዳበርና ሰነዱን ለማጠናከር ጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ሁሉም የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ በማበርከት የታቀደው ዓላማ ከግብ እንዲደርስ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
“የምንሠራው ሥራ ችግር የማይፈታ ከሆነ ትርጉም የለውም” ያሉት አቶ ኦልቀባ፣ ችግር ፈቺና ውጤት ተኮር ሥራ ለማከናወን ቁርጠኝነትና የኃላፊነት ስሜት ወሳኝ መሆኑን በማስገንዘብ የእለቱ መርሃ ግብር ተጠናቋል።
ስለተቋማችን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት
ፌስቡክ
https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p/
ቴሌግራም
http://t.me/mowieethiopia
ዌብሳይት
http://mowe.gov.et
X/ትዊተር
https://x.com/mowe_ethiopia
ዩቱዩብ
https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s
ቲክቶክ
tiktok.com/@mowetikto